በወላይታ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አስራ አንድ ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Wolaita Zone
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ካዎ ካይሻ ወረዳ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አስራ አንድ ሰዎች መሞታቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ አስታወቁ።
በወረዳው ጤፓ ቀበሌ ትናንትና ሐምሌ 29/ 2016 ዓ.ም ማለዳ ለሰዓታት የዘነበውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ የተከሰተው ናዳ የነዋሪዎች ህይወት መቅጠፉን አስተዳዳሪው ሕዝቅኤል ጎቶሮ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከሞቱት አስራ አንድ ነዋሪዎች ውስጥ የስድስቱን አስክሬን ማውጣት ቢቻልም ዝናቡ ባለማባራቱ እንዲሁም አዳዳዲስ ናዳዎች በመከሰታቸው የፍለጋውን ስራ እንደገቱት ገልጸዋል።
“ነዋሪዎች ሌሎቹን አስክሬኖች ለማውጣት በስፍራው በሚገቡበት ወቅት አዳዲስ ናዳዎች እየተከሰቱ በመሆኑ ፈታኝ አድርጎታል። ሌላ አደጋ እንዳይከሰት እና ተጨማሪ ኃዘን እንዳይመጣ በሚል ፍለጋውን አቁመነዋል” ብለዋል።
የቀሪዎቹን አስክሬን የማውጣት ስራ ዛሬ ሐምሌ 30/ 2016 ዓ.ም እንደሚከናወንም አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በተከሰቱ ሁለት ሁለት ተከታታይ የመሬት መንሸራተቶች አደጋ ከ250 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል።
በመጀመሪያው መንሸራተት ተቀብረው የነበሩ ሰዎችን ከናዳው ለማውጣት እየተደረገ በነበረው ርብርብ መሬቱ ተደርምሶ ተጨማሪ ናዳ በማስከተሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ላይ አርፎ የበርካቶችን ህይወት ቀጥፏል።
በአሁኑ ወቅት በዞኑ በተለያዩ ቀበሌዎች የመሬት መንሸራተት ስጋት ባለባቸው ስፍራ የሚኖሩ ነዋሪዎችን በትምህርት ቤቶች ፣ በእምነት ተቋማት እና በየዘመድ አዝማዱ እንዲጠለሉ እየተደረጉ መሆኑንም አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
እስካሁንም ድረስ 153 የሚሆኑ አባወራዎች ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያዎች ሰፍረዋል ብለዋል።
በዞኑ የመሬት መንሸራተት አደጋ በተለያየ ጊዜ የሚያጋጥም ሲሆን ቅዳሜ፣ ሐምሌ 27/ 2016 ዓ.ም አንድ መኖሪያ ቤት ላይ ናዳ ወርዶ አንዲት የ11 ዓመት ታዳጊ የሞተች ሲሆን የታዳጊዋም እናቷ ተጎድታ ህክምና እርዳታ እየተደረገላት እንደሚገኝም አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደምም በ2013 ዓ.ም አራት ሰዎች የሞቱበት፣ በ2005 11 ሰዎች የሞቱበት እንዲሁም በ1989 ዓ.ም 15 ሰዎች የተቀጠፉበት የመሬት መንሸራተቶች ማጋጣማቸውንም ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት፣ ዩኤንኦቻ መረጃ ከሆነ ደቡብ ኢትዮጵያ ባለፉት ወራት በከባድ ዝናብ እና በጎርፍ ከተጠቁ የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው።
በደቡብ ኢትዮጵያ የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋዎች የሚከሰቱ ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 2016 ከባድ ዝናብ ባሰከተለው የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ቢያንስ 50 ሰዎች ሞተዋል።












