ሐሰተኛ የፍቅር ግንኙነት በመፍጠር አሜሪካውያን አዛውንቶችን 8 ሚሊዮን ዶላር ያጭበረበረው ጋናዊ ታሰረ

የፎቶው ባለመብት, ABUTRICA/INSTAGRAM
ሐሰተኛ የፍቅር ግንኙነት በመጀመር አሜሪካውያን አዛውንቶችን 8 ሚሊዮን ዶላር በማጭበርበር የተጠረጠረው ጋናዊ ተጽዕኖ ፈጣሪ ፍሬድሪክ ኩሚ በቁጥጥር ሥር ዋለ።
'አቡ ትሪካ' በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) በመጠቀም የተለያዩ ሐሰተኛ የበይነ መረብ ማንነቶች እንደፈጠረ ዐቃቤ ሕግ ይፋ አድርጓል።
በማኅበራዊ ሚዲያ እና ፍቅረኛ በሚያገናኙ መተግበሪያዎች ላይ የተዋወቃቸውን አዛውንቶች ዒላማ ማድረጉ ተገልጿል።
ከእነዚህ ሰዎች ጋር የፍቅር ግንኙነት የጀመረ በማስመሰል ገንዘብ ሲቀበልም ነበር።
በበይረ መረብ የገንዘብ ማጭበርበር ለመፈጸም በመመሳጠር እና ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ መስመር በማስገባት በአሜሪካ እንደሚከሰስ ተገልጿል።
ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ 20 ዓመት እስራት ይፈረድበታል።
የ31 ዓመቱ ፍሬድሪክ ኩሚ የአሜሪካ እና የጋና የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት የጋራ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ሥር ውሏል። አሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጣት የምትጠይቅም ይሆናል።
እስካሁን ድረስ ፍሬድሪክ ስለ ጉዳዩ አስተያየት አልሰጠም።
'ኢማኑኤል ኮጆ ባ ኦቤንግ' የሚል ሌላ መጠሪያ ያለው ፍሬድሪክ፤ በኢንስታግራም 100,000 ተከታዮች አሉት። ቅንጡ ቤቱን በማኅበራዊ ሚዲያ በማሳየትም ይታወቃል።
ስለ ገቢው ጥያቄ መነሳት የጀመረው በእነዚህ ቅንጡ ቤቶች ምክንያት ነው።
ዐቃቤ ሕግ "በስልክ፣ በኢሜል እና በአጭር የጽሑፍ መልዕክት አማካኝነት ከተጎጂዎቹ ጋር ቅርርብ በመፍጠሩ አምነውታል" ብሏል።
"ከዚያም ግንኙነቱን በመጠቀም ድንገተኛ ሕክምና አልያም ጉዞ ገጠመኝ ወይም ደግሞ ኢንቨስት ማድረግ እፈልጋለሁ በሚል ገንዘብ አጭበርብሯል" ሲልም አክሏል።
ፍሬድሪክ በአሜሪካ እና በጋና ተባባሪዎች የነበሩት ሲሆን፤ በማጭበርበር የተገኘው ገንዘብ ወደ ሦስተኛ ወገን እንዲተላለፍ ተደርጓል።
አሜሪካ ግለሰቡን የምትከስሰው አረጋውያንን ከጥቃት ለመከላከል በወጣው ሕግ አማካኝነት ነው።
አረጋውያን አሜሪካውያን ላይ የሚደርሰውን ማጭበርበር ለመግታት አገሪቱ በምዕራብ አፍሪካ የምትወስደውን እርምጃ አጠናክራ ቀጥላለች።
በያዝነው ዓመት መባቻ በሐሰተኛ የፍቅር ግንኙነት ስም ገንዘብ መዝብሯል በሚል ዳዳ ጆይ ሪሚክስ የተባለ ጋናዊ በቁጥጥር ሥር ውሎ ለአሜሪካ ተላልፎ ተሰጥቷል።
በያዝነው ወር ደግሞ ኦልዋሱን አድኮያ የተባለ ናይጄሪያዊ 20 ዓመት እንዲታሰር በአሜሪካ ፍርድ ቤት ተወስኗል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የባንክ ገንዘብ በማጭበርበር እንዲሁም 2 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ መስመር በማስገባት ነበር የተከሰሰው።















