የአሜሪካዋ ግዛት ከዕጸ ፋርስ ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ ለተባሉ 175 ሺህ ግለሰቦች ምህረት አደረገች

የአሜሪካዋ ግዛት ሜሪላንድ ገዥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካዋ ግዛት ሜሪላንድ ገዥ ከዕጸ ፋርስ ጋር በተያያዙ ክሶች ጥፋተኛ ተብለው ለተፈረደባቸው 175 ሺህ ግለሰቦች ምህረት አደረጉ።

የግዛቷ አስተዳዳሪ እንዳሉት ይህ እርምጃቸው አገራቸው “በአደንዛዥ ዕጾች ላይ ጦርነት በሚል ለአስርት ዓመታት የፈጸመቻቸውን ጥፋቶች” ለማቃናት ነው ብለዋል።

አስተዳዳሪው ዌስ ሙር ትዕዛዛቸው በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ትልቁ ምህረት የተደረገለት አኃዝ እንደሆነም ጠቅሰው በአገሪቱ የተወሰደ ታሪካዊ እርምጃም እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።

“ሜሪላንድ ይህንን በመጠቀም ታሪካዊ ስህተቶችን የማስተካከል ሂደት ላይ ናት” ብለዋል።

ለተለያዩ ህመሞች ጥቅም እንዳለው የተለያዩ ሳይንሳዊ ምርምሮች ያረጋገጡት ዕጸ ፋርስ (ካናቢስ)ን በሜሪላንድ ህጋዊ ከሆነ አንድ ዓመት አስቆጥሯል። በሜሪላንድ ብቻ ሳይሆን በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች ዕጸ ፋርስን ህጋዊ አድርገውታል።

የፌደራል መንግሥቱም በብሄራዊ ደረጃ ከህገወጥነት ሊያወጣ ሲሆን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከዕጹ ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ ለተባሉ ሰዎች ሁለት ጊዜ የጅምላ ምህረት አድርገዋል።

በዲሞክራቲክ ፓርቲ ውስጥ ዝናቸው እያንሰራራ ያለው የ45 ዓመቱ ፖለቲከኛ በህዝበ ውሳኔ ዕጸ ፋርስ ህጋዊ መሆኑን ተከትሎ ፍትሃዊ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰዱ ተገቢ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

“ዕጸ ፋርስን ህጋዊ ማድረጉ ለአስር ዓመታት ያህል በአደንዛዥ ዕጾች ጦርነት በሚል የተፈጸሙ ጉዳቶችን ወደኋላ ሄዶ አያስተካክልም” ሲሉም ነው ፖለቲከኛው ሰኞ እለት በሰጡት አስተያየት የተናገሩት

“ከዕጹ ጋር በተያያዘ የተወነጀሉ ሰዎችን ማየት እስካልቻልን ድረስ የህጋዊነቱን ጥቅም ልንደሰትበት አንችልም” ሲሉም ተደምጠዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት የወጣ የመንግሥት ሪፖርት እንደሚያሳየው ነጭ የሜሪላንድ ግዛት ነዋሪዎች ከጥቁሮች በበለጠ ዕጸ ፋርስን ቢጠቀሙም ህጋዊ ከመሆኑ በፊት የሚታሰሩ ጥቁሮች ቁጥር ሁለት ዕጥፍ መሆኑን አሳይቷል።

በአገሪቱ ውስጥ ያለው የጥቁር ወንዶች እስረኛ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ያሳየው ይህ መረጃ በአማካኝም ከሶስቱ ሁለቱ ጥቁር ወንዶች መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።

ከረዥም ጊዜ በፊት መወሰድ የነበረበት ይህ እርምጃ በዘር ላይ ያተኮረ መድልዎ ሲፈጸምበት የነበረውን የዕጸ ፋርሱን “ዘመናዊ ባርነት” ሊያስወግድ እንደሚችል የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቡ ህግ አንቶኒ ብራውን ተናግረዋል።

ምህረቱ ከዕጸ ፋርስ ጋር በተያያዘ በፍርድ ቤት የተመዘገቡ ክሶችን ነጻ በማድረግ ይፍቃል። እንዲሁም ከዕጸ ፋርስ ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ ተብለው ህይወታቸው ያለፉ ሰዎችንም ነጻ ያደርጋል።