ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤርትራ እራሷን በማግለሏ ለቻን ማጣሪያ ከኢትዮጵያ ቡድን ጋር የነበራት ግጥሚያ ተሰረዘ
በአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ቡድኖች ሻምፒዮና ወይም በቻን ውስጥ ለመሳተፍ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ሊያደርጉት የነበረው ግጥሚያ ተሰረዘ።
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ብሔራዊ ቡድኖች ከሜዳቸው ውጪ የደርሶ መልስ ጨዋታቸውን በደቡብ ሱዳን ዋና መዲና ጁባ ጥቅምት 21 እና ጥቅምት 24/2017 ዓ.ም. ሊያካሄዱ መረሃ ግብር ተይዞላቸው ነበረ።
ነገር ግን ኤርትራ ከውድድሩ ራሷን ማግለሏን ተከትሎ ጨዋታው መሠረዙን የአፍሪካ እግር ኳስ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ካፍ አሳውቋል።
የ2025 የቻን ማጣሪያ ውድድር መርሃ ግብር በሚቀጥለው ሳምንት ይካሄዳል ተብሎ የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጨዋታቸውን በሦስተኛ አገር ሜዳ እንዲያደርጉ ቀጠሮተይዞላቸው ነበር።
የሁለቱ አገራት የመጀመሪያው ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታድየም ሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ ታንዛኒያ ይካሄዳል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ሁለቱም ጨዋታ ደቡብ ሱዳን ላይ እንደሚከናወን ዘግይቶ የወጣ መረጃዎች ጠቁመው ነበር።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካ እግር ኳስ የበላይ አካል ካፍ መስፈርት የሚያሟላ ስታድየም የላቸውም።
በአገር ውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ ተጨዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የቻን አፍሪካ ዋንጫ ከአውሮፓውያኑ የካቲት 1 እስከ 28/2025 ይካሄዳል።
ቻን በሦስት የምሥራቅ አፍሪካ አገራት የሚካሄድ መሆኑን ካፍ አረጋግጧል።
ውድድሩን ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ እንደሚያዘጋጁት የካፍ ፕሬዝደንት ፓትሪስ ሞትሴፔ አሳውቀዋል።
ኤርትራ ነፃነቷን ካወጀች በኋላ የውድድር ጨዋታ አድርገው የማያውቁት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለግጥሚያው እየተዘጋጁ መሆናቸው ተገልጾ ነበር።
በቅርቡ የተሾሙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለማጣሪያው ጨዋታ የመለመሏቸውን ተጫዋቾች ጠርተዋል።
ከኤርትራ ጋር የሚደረገው ጨዋታ በጁባ ስታድየም የሚደረገው የካፍን መስፈርት የሚያሟሉ ስታድየሞች ባለመኖራቸው ይሁን በሌላ ምክንያት የሚታወቅ ነገር የለም።
ኢትዮጵያ ከኤርትራ እንደምትጫወት ይፋ የተደረገው በግብፅ መዲና ካይሮ በተካሄደው የዕጣ ድልድል ሥነ-ሥርዓት ነው ።
ኤርትራ በቻን ውድድር ከተሳተፈች በርካታ ዓመታት አስቆጥራለች።
አልፎም የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን በሌሎች የማጣሪያ ውድድሮች መሳተፍ ካቆመ ቆይቷል።
አሁን በሚቀጥለው ሳምንት እሁድ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው ግጥሚያ ከመሰረዙ ውጪ ኤርትራ ከውድድሩ እራሷን እንድታገል ያደረጋት ምክንያት አልተገለጸም።
በዚህም ምክንያትኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታ ሳታደርግ ከሱዳን እና ከታንዛኒያ አሸናፊ ጋር ቀጣይ ጨዋታዋን ታደርጋለች።