የአሜሪካ የኢሚግሬሽን ኃላፊዎች በአይስ ስለተገደሉት አሜሪካውያን ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፕሬዚዳንት ትራምፕ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኢሚግሬሽን ተቆጣጣሪዎች ስለተገደሉ ሁለት አሜሪካውያን አስተያየታቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ።
የአስተዳደሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኮንግረንስ ፊት ቀርበው ጥያቄ በቀረበላቸው ወቅት የፕሬዚዳንቱን የኢሚግሬሽን አጀንዳ በመደገፍ ተከላክለዋል።
ከኮንግረሱ ሕግ አውጪዎች ጠንካራ ጥያቄዎች የቀረበላቸው ባለሥልጣናቱ፣ ተቃዋሚ ሠልፈኞች ጠብ አጫሪ ትርክቶችን በተቆጣጣሪዎቹ ላይ እንደሚያነሳሱ እና ኤጀንሲዎቹ እርምጃዎች ከመውሰድ ወደ ኋላ እንደማይሉ ተናግረዋል።
የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ተቆጣጣሪ (አይስ) ተጠባባቂ ኃላፊ ቶድ ላዮንስ "ሊያስፈራራን እንደሚችል ለሚያስቡ ሁሉ መልዕክት አለኝ። አይሳካላችሁም" ብለዋል።
ባለሥልጣናቱ ኮንግረስ ፊት ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡ የተደረገው የአይስ መኮንኖች ሁለት አሜሪካውያንን መግደላቸውን ተከትሎ ነው።
አሌክስ ፕሬቲ እና ሬኔ ጉድ የተባሉት አሜሪካውያን በሚኒያፖሊስ በኢሚግሬሽን እና ጉሙሩክ ተቆጣጣሪዎች መገደላቸውን ተከትሎ ሕዝባዊ ቁጣ ተቀስቅሶ ነበር።
የጉሙሩክ እና ድንበር መከላከል ኮሚሽነሮች ላዮንስ እና ሮድመኒ ስኮት በሚኒያፖሊስ ከሚካሄደው ቀጣይነት ያለው እንቅስቃሴ ባሻገር ወደፊት በመላው አሜሪካ ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ተሳትፎ ያደርጉ እንደሆን ተጠይቀዋል።
አብዛኛው ጥያቄ ያተኮረው የአይስ መኮንኖች ካሜራ በልብሳቸው ላይ እንዲገጠም የሚያዘው አዲሱ ፖሊሲ ላይ ነበር።
ባለሥልጣናቱ አስተዳደሩ በሚኒሶታ የወሰደውን እርምጃ በመደገፍ ተከላክለዋል። አክለውም በካሜራ የተቀረጸው ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ጠይቀዋል።
የአገር ውስጥ ደኅንነት መስሪያ ቤት ኃላፊዋ ክርስቲ ኖኤም የአይስ መኮንኖች ካሜራ ልብሳቸው ላይ ይገጠምላቸዋል ሲሉ ካስታወቁ በኋላ ከ3000 በላይ መኮንኖች ካሜራውን መረከባቸውን ሊዮንስ ተናግረዋል።
ስድስት ሺህ ያህሉ ካሜራውን ማድረግ ይጀምራሉ ያሉት ኃላፊው 13 ሺህ የአይስ መኮንኖች በሥራ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ስኮት ምን ያህል የጉሙሩክ እና ድንበር ጠባቂ መኮንኖች ካሜራ እንዳላቸው ባይናገሩም ከ20ሺዎቹ መካከል 10 ሺህ መኮንኖች ይኖራቸዋል ሲሉ ግምታቸውን ተናግረዋል።
"እዚህ እየተነጋገርን እያለ ፕሮግራሙን እየገነባን ነው' ሲሉ ተናግረዋል።
የኢሚግሬሸን መኮንኖች ካሜራ በልብሳቸው ላይ ይገጠምላቸው የሚለው ሃሳብ የመጣውም አሌክስ ፕሬቲ እና ሬኔ ኒኮል ጉድ በሚኒያፖሊስ መገደላቸውን ተከትሎ ነው።
ባለሥልጣናቱ መኮንኖቹ በከተማዎች ተሰማርተው በሚገኙበት ወቅት ስለሚለብሱት የፊት ጭምብል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
ሊዮን መኮንኖቹ ጭምብላቸውን እንዲያወልቁ ያደርጉ እንደሆን ተጠይቀው እንደማያደርጉ ተናግረዋል።
ሊዮንስ አሜሪካውያን ዒላማ ተደርጎባቸዋል በሚል የቀረበላቸውን ጥያቄ አስተባብለው አንድም አሜሪካዊ ሆን ተብሎ በቁጥጥር ሥር አልዋለም ሲሉ ተከላክለዋል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ግን በርካታ አሜሪካውያን በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ዘግበዋል።















