በአይስ ቁጥጥር ሥር ያለ የ5 ዓመት ሕፃን እንዲለቀቅ አሜሪካዊው ዳኛ አዘዙ

የ5 ዓመቱ ሕፃን ሊያም ኮኔሆ ራሞስ የትምህርት ቤት ቦርሳ ተሸክሞ፤ ሰማያዊ ቆብ ጭንቅላቱ አድርጎ፤ ለደኅንነቱ ሲባል ፊቱ እንዳይታይ ተደርጓል

የፎቶው ባለመብት, Columbia Heights Public Schools

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አሜሪካዊው ዳኛ የ5 ዓመቱ ሕፃን እና አባቱ ቴክሳስ ከሚገኘው የስደተኞች ማቆያ ማዕከል እንዲለቀቁ ትዕዛዝ አስተላለፉ።

ሊያም ኮኔሆ ራሞስ የተባለው የ5 ዓመት ሕፃን ሚኒያፖሊስ ከሚገኘው ቤቱ በስደተኛ ተቆጣጣሪ ፖሊሶች (አይስ) ቁጥጥር ሥር መዋሉ በመላው አሜሪካ ቁጣን ቀስቅሷል።

የሕፃኑ አባት አድሪያን አሌክሳንደር ኮኔሆ አሪያስም በቁጥጥር ሥር ውሏል።

ባለሥልጣናት ሕፃኑ በቁጥጥር ሥር የዋለው አባቱ "ሕጋዊ ወረቀት የሌለው በመሆኑ" እና በወቅቱ "ሕፃኑን ጥሎት በመሄዱ" ነው ብለው "ሕፃናትን ዒላማ አናደርግም" የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

ቅዳሜ እለት አሜሪካዊው ዳኛ ፍሬድ ቢዬሪ ከቤተሰቦቹ ጠበቃዎች በቀረበላቸው ጥያቄ መሠረት የመንግሥት ባለሥልጣናት ሕፃኑ እና አባቱን በመጪው ማክሰኞ እንዲለቋቸው ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

"ይህ ጉዳይ በክፉ ሐሳብ የተነሳውን እና ደካማ አፈፃፀም ያለውን መንግሥት ስደተኞችን ለማባረር የሚያደርገው እንቅስቃሴ ማሳያ ነው፤ ምንም እንኳን ሕፃናት ላይ ጉዳት ቢያደርስም" ሲሉ ዳኛው ውሳኔ ባስተላለፉበት ፅሑፍ ተናግረዋል።

በቀድሞው ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን የተሾሙት ዳኛ ስደተኞችን ማባረር ሥርዓት ባለው እና ሰብዓዊ በሆነ መንገድ እንጂ አሁን እየሆነ ባለው ሁኔታ መሆን የለበትም ብለዋል።

ቢቢሲ ጉዳዩን በተለመከተ የሀገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስቴርን አስተያየት ጠይቋል።

የቤተሰቡ ጠበቃ የሆኑት ማርክ ፕሮኮሽ፣ሕፃኑ እና አባቱ ቴክሳስ ግዛት ሳን አንቶኒዮ ከተማ በሚገኝ ማቆያ ውስጥ እንዳሉ አረጋግጠዋል።

ጠበቃው እንዳሉት ሕፃኑ እና አባቱ በአውሮፓውያኑ 2024 ከኤኳዶር ወደ አሜሪካ የመጡ ሲሆን ጥገኝነት ጠይቀው ትክክለኛውን አካሄድ እየተከተሉ ቆይተዋል።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የትራምፕ አስተዳደር በሚኒሶታ ግዛት የሚያደርገውን ስደተኞችን የማባረር እንቅስቃሴ ገታ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

በሚኒያፖሊስ ከተማ በተቀሰቀሰ ፀረ-አይስ ሰልፍ ምክንያት ሁለት አሜሪካዊያን መገደላቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሷል።

ታኅሣሥ መግቢያ ላይ ረኔ ጉድ የተባለችው የ37 ዓመት ሴት በስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት የፀጥታ ባልደረቦች ስትገደል ባለፈው ሳምንት ደግሞ አሌክስ ፕሬቲ የተባለው ግለሰብ መገደሉ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቷል።

ረኔ ጉድ ከተገደለች ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አሌክስ ፕሬቲ የተባለ አሜሪካዊ ከአይስ ፖሊሶች ጋር ተጋጭቶ በጥይት ተመትቶ መሞቱ በሚኒያፖሊስ ከተማ ያለው ተቃውሞ እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል።

ቅዳሜ ከሚኒያፖሊስ በተጨማሪ በኒው ዮርክ፣ሎስ አንጀለስ፣ ቺካጎ እና ዋሽንግተን ዲሲን ጨምሮ በተለያዩ የአሜሪካ ከተማዎች ተቃውሞዎች ተካሂደዋል።

የሰልፉ አዘጋጆቹ አሜሪካውያን ከሥራ እና ከትምህርት ቤት በመቅረት ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ አቅርበዋል።