“ልንበላው የዘራነውን እህል አፈር በላው፤ በረሃብ ልንሞት ነው” የትግራይ አርሶ አደሮች

እርጅናና መከራ የተፈራረቀባቸው አርሶ አደር አቶ ገብረመድህን ገብረማርያም
የምስሉ መግለጫ, እርጅናና መከራ የተፈራረቀባቸው አርሶ አደር አቶ ገብረመድህን ገብረማርያም

የአሁኑን አያደርገው እና በትግራይ ክልል ምሥራቃዊ ዞን የሚገኘው የአጽበደራ ወረዳ ቀድሞ እህል የተትረፈረፈበት፣ እንስሳት በስፋት የሚታዩበት ለም አካባቢ ነበር።

ስንዴ እና በቆሎ በብዛት የሚበቅልበት ይህ አካባቢ በማር ምርቱም ታዋቂ ነበር።

አሁን መሬቱ ጦም ካደረ ሰነባበተ።

ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ማክተሙን ተከትሎ አርሶ አደሮች ወደ እርሻቸው ቢመለሱም በድርቅ ምክንያት ለከፋ የምግብ እጥረት ተዳርገዋል።

እርጅና እና መከራ የተፈራረቀባቸው አርሶ አደር ገብረመድኅን ገብረማርያምን ቢቢሲ ያገኛቸው በደጃፋቸው ከተቀመጠ ያልተወቃ ትንሽ የባቄላ ክምር ፊት ተቀምጠው ሲቆዝሙ ነው።

በአካባቢያቸው ያጋጠመውም ድርቅ ምን ያህል የከፋ እንደሆነም ሲናገሩ በሐዘን ነው።

“ሦስት፣ አራት የእርሻ ማሳ ጠፍቷል። ይህ የምታየው ከአንድ ማሳ የተሰበሰበ ነው። የሚሸጥም፣ የሚለወጥም የለንም “ ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በአምላክ እና በመንግሥት እጅ ላይ ወድቀናል። እርስ በርስ እየተበዳደርን ከረምን እንጂ የምንበላውም የምንጠጣውም የለንም” ይላሉ።

አቶ ገብረመድኅን ከአራት ልጆቻቸው እና ከአራት የልጅ ልጆቻቸው ጋር በባዶ ቤት ከረሃብ ጋር ተፋጠዋል።

አርሶ አደሩ የሚኖሩበት ገብረኪዳን ተብሎ የሚጠራ ቀበሌ ለአመል እንኳን ውሃ ያቆረበት ኩሬ እንኳን አይታይም። በአካባቢው የሚገኘው ግድብ ውሃ አርፎበት የሚያውቅ እንኳን አይመስልም።

በዐይን የሚታይ ሳር በሌለበት ሜዳ የሚርመሰመሱት ከብቶች ሲታዩ ‘አፈር የሚልሱ’ ናቸው ይላሉ።

አቶ ገብረመድኅን ምሬታቸው ጥልቅ ነው።

“እግዚአብሔር በሰኔ አንድ ዝናብ፣ በሐምሌም አንድ ዝናብ ብቻ ሰጥቶ አጥፍቶናል” ይላሉ።

“ያየኸውን ባቄላ ቀቅለን ከልጆቻችን ጋር ለአንድ ሁለት ቀን እራት ቢሆነን ነው። ዘር እስኪዘራ ድረስ ማን ያቆየዋል?” ሲሉም ይጠይቃሉ።

ወደ በረቱ እያመላከቱም “ከብቶቻችንም ተጎድለዋል” ይላል ተስፋ በቆረጠ ድምጽ።

“ጓሮውም እንደምታየው ነው፤ ባዶ ነው ያለው። ሁሉም ችግር ነው በአንድ ላይ እኛ ላይ የወረደው” ይላሉ።

ወ/ሮ ለተስላሴ
የምስሉ መግለጫ, ወ/ሮ ለተስላሴ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወ/ሮ ለተሥላሴ ደስታ የአቶ ገብረመድኅን ጎረቤት ናቸው።

ሰውነታቸው በረሃብ ተጎሳቁሎ የጠዋት ፀሐይ ሲሞቁ አገኘናቸው።

“ልጄ ሞቶብኛል፤ እኔም በረሃብ ልሞት ነው። የሚጦረኝ ልጄ ሞቶብኛል። ካሕሳይ ገብረጻድቃንን የማያውቅ የለም። አራት ነው የወለድኩት። ታጋዩ ልጄ አንድ ልጅ ብቻ ነው የወለደው” ይላሉ በጦርነቱ የተሰዋ ልጃቸውን በከፋ ሐዘን በማስታወስ።

ወ/ሮ ለተሥላሴ ባለቤታቸውንም በሞት አጥተዋል።

ከልጆቻቸው ጋር የሚኖሩት እኚህ እናት ይባስ ብሎ ማሳቸው ምንም እህል አላበቀለም።

“ልጄ ጎበዝ ነበር። ማሳውን የሚያርስልኝ እሱ ነበር። ሴቷ ልጄም ፀጉር ትሠራ ነበር። እነዚህ የምታያቸው የልጅ ልጆቼ ናቸው። ልጄ ከሞተ በኋላም እሷም ታመመች፤ እሷ ሠርታ ትጦረኝ ነበር። አሁን ሐዘኑ ተደማምሮብኝ በረሃብ ልሞት ደርሻለሁ” ይላሉ የተስፋ መቁረጥ ሳግ እየተናነቃቸው።

ሌላኛዋ የአካባቢ ነዋሪ እና ዐይነ ስውር የሆኑት ወ/ሮ ፀጋ ሰበሆ፣ ረሃብ ተጨምሮባቸው አልጋ ላይ ወድቀዋል።

ዕድሜያቸውን በትክክል ባያውቁትም ‘ጣልያን ተሸንፎ ሲወጣ፣ በእንግሊዝ ጊዜ ተወለድኩ” ይላሉ።

“ዐይነ ስውርነቴን ይዤ ከቤት እንዳልወጣ አካሌ ተሰብሯል። ጉልበቴን ረሃብ ሰብሮታል። ተነስ ብለው አይነሳም። ይኸው እንደታጠፍኩ አለሁ” ሲሉም ሐዘናቸውን ይገልጻሉ።

“የተዘራው አሯል። ልንበላው ብለን የዘራነው አፈር በልቶታል። እንደዚህ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም” ይላሉ ስቃይ በተሞላ ድምጽ።

ወ/ሮ ፀጋም ልክ እንደ ሌሎቹ ነዋሪዎች በልጆቻቸው ነው የሚጦሩት።

“ኪዳነ ምኅረት እናቴ! ይህንን እንዳይ ነው ያቆየሺኝ?” እያሉ በመቆዘም የሕይወታቸው ፍጻሜ ይጠባበቃሉ።

ቢቢሲ በጎበኛቸው የአጽበደራ አካባቢዎች ነዋሪዎች ምንም ባይኖራቸውም ‘አረ ቤት ግባ!’ ማለት ልማዳቸው ነው።

የሚላስ የሚቀመስ በሌለበት እንግዳን ‘ብላ ጠጣ’ ብለው ባለመጋበዛቸው ግን ይቆጫሉ።

እርጅናና መከራ የተፈራረቀባቸው አርሶ አደር አቶ ገብረመድህን ገብረማርያም
የምስሉ መግለጫ, እርጅናና መከራ የተፈራረቀባቸው አርሶ አደር አቶ ገብረመድህን ገብረማርያም

ቀበሌ ሐድነትም በድርቅ ከተጎዱ የአጽበደራ አካባቢዎች አንዱ ነው።

አለቃ ፍሰሐ ገብረኪዳንም የዐይናቸውን ብርሃን አጥተው ቤት ተቀምጠዋል። የ80 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ናቸው ።

“ኅዳር እና ታኅሣሥ እሸት ሳናይ ነው ያለፉት” ይላሉ ያሉበትን አሳሳቢ ሁኔታ ሐዘን በተጫነው ድምጽ ሲያስረዱ።

“ባለቤቴ እንደምንም ብላ እየጦረቺኝ ነው። ከክረምት ወጥተን ወደ ክረምት ነው የገባነው። ሞትን እየጠበቅን ነው። ሞትስ የነበረ ነው። ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚሉት በረሃብ ከመሞት በጦርነት መሞት ይሻላል።”

“ልጆቻችን ተበታትነዋል” አሉ እንባ እየተናነቃቸው።

“ጎተራ፣ አቁማዳው የለም። ቁራሽም የለን፣ እግዜርን አልመታው። ባለቤቴ ከየት እነንደምታመጣው እንጃ የትም ብላ ያገኘችውን ታቀርብልኛለች። እስካሁን ቁራሽም ብትሆን ሳትሰጥ ጾሜን አላሳደረቺኝም። አንድ በሬ ነበረን፤ በመስከረም ሸጥነው “ በማለት የባለቤታቸው ቤተሰቡን በሕይወት ለማቆየት የሚያደርጉትን ጥረት ገልጸዋል።

ሆኖም “በእኔ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ላይ የወረደ መከራ ነው” ብለው ደግሞ ራሳቸውን ያጽናናሉ።

ድርቅ ያጠቃው የአጽበደራ ወረዳ
የምስሉ መግለጫ, ድርቅ ያጠቃው የአጽበደራ ወረዳ

በአካባቢው በችግር ላይ ለሚገኙት ነዋሪዎች የሚቀርብ እርዳታ ብሎ ነገር እንደሌለ እና ቢኖር ግን ከሚያገኙት መካከል ሊሆኑ ይችሉ እንደነበር ይገልጻሉ አቶ ፍስሐ ።

በከፍተኛ ረሃብ ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት የሚሄድ ሕጻናት የሉም።

የአጽበደራ አርሶ አደሮች የዝናብ እጥረት ባስከተለው ድርቅ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ ተደቅኖባቸዋል። የወረዳው መሬት ደርቆ ነዋሪዎቹን መመገብ አልቻለም።

እርዳታ በአስቸኳይ ካልደረሰላቸው፣ በሞት አፋፍ ያሉት ነዋሪዎች ወደ መቃብር መውረዳቸው ነው።

የአጽቢ ወረዳ፣ 12 ቀበሌዎች ያሉት ሲሆን ዘጠኙ በድርቅ ክፉኛ እንደተጎዱ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ መዝገበ ግርማይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በድርቁ ምክንያት እስካሁን 111 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። የድርቁ መነሻ የዝናብ እጥረት ነው። ባለፈው ዓመት ክረምት መደበኛ ዝናብ አልነበረም። ሁለት ጊዜ ብቻ ነው የዘነበው። እሱም ካፊያ ብቻ ነበር።

“በዚህ ምክንያት የተዘራው ማሳ ላይ እንዳለ ተገልብጧል። ወትሮም ድርቅ የሚያጋጥም ቢሆንም፣ የዚህ ዓመቱ ግን የተለየነ ነው። በዕድሜያችን ሙሉ እንደዚህ ዓይነት ድርቅ አይተንም ሰምተንም አናውቅም።”

ከዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ይቀርብ የነበረው እህል ከተቋረጠ 10 ወራት ተቆጥረዋል።

በክልሉ እንዲሁም በአገሪቱ በረሃብ ለተጎዱ ሰዎች የተላከን ዕርዳታ መጠነ ሰፊ ዝርፊያ በመፈጸም ሽያጭ ላይ ውሏል በሚል የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤአይዲ የሚያቀርቡትን የምግብ እርዳታ ማቆማቸው የሚታወስ ነው።

በዚህም ውሳኔ ምክንያት በትግራይ የሚገኙት የእርዳታ ድርጅቶቹ መጋዝኖች በእርዳታ እህል ተሞልተው እያለ ነዋሪዎች ግን በረሃብ እያለቁ ነው።

ድርቅ ያጠቃው የአጽበደራ ወረዳ
የምስሉ መግለጫ, ድርቅ ያጠቃው የአጽበደራ ወረዳ