ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የንግሥት ኤልዛቤጥን አስክሬን ለመሰናበት ረዥም ሰልፍ ይኖራል ተባለ
የዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ አስክሬንን ለመሰናበት የሚፈልጉ ሰዎች ረዥም ሰልፍ ሊጠብቃቸው እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ተሰጠ።
በዌስትሚኒስተር ቤተ-መንግስት ውስጥ በሚካሄደው የሸኝት መርሃ ግብር ዙሪያ ዝርዝር መረጃዎች ይፋ ተድርገዋል።
ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በመርሃ ግብሩ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል። በታሪካዊው የሽኝት መርሃ ግብር ላይ ለመካፈል የሚፈልጉ ሰዎች ለሰዓታት አልፎ ተርፎም ምሽቱን ለመጠበቅ ሊገደዱ ይችላሉ ተብሏል።
ሰዎች ምግብና መጠጥ እንዲሁም ተስማሚ ልብስ ይዘው እንዲመጡ ተጠይቀዋል።
የሽኝት መርሃ ግብሩ ረቡዕ ዕለት ጀምሮ ሰኞ የቀብር ስነ ስርዓቱ እስኪከናወን ይቀጥላል።
በእነዚህ ቀናትም የሽኝት መርሃ ግብሩ ለ24 ሰዓት ክፍት ይሆናል።
በአዳራሹ የተሸኙ የመጨረሻው የንጉሣዊ ቤተሰብ አባል የዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ እናት ሲሆኑ እአአ በ2002 ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች ተገኝተዋል።
የዌስትሚኒስተር ዲን እንዳሉት የንግሥቲቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት “በተግባር የሚኖር ሕያው ባህል” ይሆናል።
የተከበሩ ዶ/ር ዴቪድ ሆዬል “የምናመሰግንበት ዕድል ነው… እናም ሃዘናችንን ለመግለጥ ጥሩ ዕድል ነው” ብለዋል።
ንግሥቲቱ ሐሙስ ዕለት ባልሞር በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ማረፋቸው ከተነገረ በኋላ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሐዘንተኞች ባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት፣ ሳንድሪንግሃም ሃውስ እና ዊንዘር ቤተ-መንግስትን ጨምሮ ንግስቲቱ በሚወዷቸው ቦታዎች አበባ በማስቀመት ሃዘናቸውን እየገለጹ ነው።
የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በለንደን ከመፈጸሙ በፊት አስከሬን እሑድ ዕለት ከባልሞር ወደ ኤድንበራ ሲጓዝ ለማየት ብዙ ሰዎች ተሰብስበዋል።
ሰኞ ዕለት የንጉሣዊው ቤተሰብ አባላት አስክሬኑን በማጀብ ስኮትላንድ ከተማ ወደሚገኘው የቅዱስ ጊልስ ካቴድራል ይጓዛሉ። የንግሥቲቱ አስከሬን በካቴድራሉ ለ24 ሰዓታት ይቆያል።
በዚሁ አጋጣሚ ሰዎች በቦታው በመገኘት ሃዘናቸውን መግለጽ ይችላሉ ተብሏል። በመቀጠልም አስከሬኑ ወደ ባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ያመራል።
በሸኝት መርሃ ግብሩ ወቅት የንግሥቲቱ የሬሳ ሳጥን በፓርላማው ውስጥ በሚገኘው ዌስትሚኒስተር አዳራሽ ውስጥ ከፍ ባለ መድረክ ላይ ያርፋል።
በዚህ መርሃ ግብር ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ሰዎች ለሰዓታት ከፍ አልያም ምሽቱን በሙሉ ወረፋ ይዘው ሊያሳልፉ ይችላሉ ተብሏል።
በአካባቢው የሕዝብ ማመላለሻ እና የመንገድ መዘጋት ሊኖር እንደሚችልም ይጠበቃል።
ጎብኚዎች በኤርፖርት ያለውን አይነት ፍተሻ የሚጠብቃቸው ሲሆን በቀላሉ የሚከፈት አንድ ቦርሳ ብቻ እንዲይዙ ተጠይቋል። ሊይዟቸው በሚችሏቸው ዕቃዎች ላይም ገደቦች ተጥለዋል።
ሰዎች በዌስትሚኒስተር ቤተ-መንግስት ውስጥ እያሉ ዝም ማለት እና ተገቢውን ልብስ በመልበስ ዝግጅቱን እንዲያከብሩ ተጠይቀዋል። "ፖለቲካዊ ወይም አፀያፊ መፈክሮች" ያለባቸው ልብሶች ተከልክለዋል።
ሰዎች ሞባይል ስልኮቻቸውን እንዲያጠፉ ወይም ድምፍ አልባ እንዲያደርጉ እና ድምጽ እንዲቀንሱ ይጠየቃሉ።
በፍተሻ ቦታ እና በዌስትሚኒስተር ቤተ መንግስት ውስጥ ቀረጻ፣ ፎቶግራፍ ማንሳት እና የሞባይል ስልኮችን ወይም ሌሎች መሳሪያዎችን መጠቀም አይፈቀድም።
ለሌሎች ሰዎች ወረፋ መያዝ የማይፈቀድ ሲሆን የግል ዕቃቸውንም የሚጠብቅላቸው ሳይኖር ትተው እንዳይሄዱ ተጠይቀዋል።
ምን መያዝ ይፈቀዳል?
- ለአየር ሁኔታ ተስማሚ ልብስ
- በወረፋ ወቅት የሚበሉ ምግቦች እና መጠጦች (ሰዎች የፍተሻ ቦታዎች ከመድረሳቸው በፊት ማስወገድ ይኖርባቸዋል)
- የስልክ ባትሪ መሞያ (ቻርጀር)
- እጅግ አስፈላጊ መድኃኒቶች ወይም መሠረታዊ የሆኑ ቁሶች
ምን መያዝ አይፈቀድም?
- ፔርሙዞች ወይም የውሃ መያዣዎች (ውስጡን የሚያሳይ የውሃ መያዣ ይፈቀዳል)
- አበቦች ወይም ሌሎች የማስታወሻ ዕቃዎች (አበባዎች ወደተዘጋጀላቸው ቦታ ይወሰዳሉ)
- ስለታም ነገሮች
- የራስን መከላከያ መሳሪያዎች
- ቀለም መርጫዎች፣ ቁልፎች፣ ሰንሰለት፣ መወጣጫ መሣሪያ እና ማንኛውም አደገኛ ዕቃዎች
- ርችቶች፣ ሌሎች ሁከት ወይም ጫጫታ ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች
- ማቀዝቀዣዎች፣ ማደናቀፊያዎች፣ ተንቀሳቃሽ ፍራሾች እና ሌሎች ተመሳሳይ መሣሪያዎች
- የማይታጠፉ ወንበሮች
ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎች ማክሰኞ ምሽት ይፋ ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።