አማጽያን አብዛኛውን የደቡብ ሶሪያን ቁልፍ ከተሞች መያዛቸው ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በደቡባዊ ሶሪያ የሚገኙ አማፂ ኃይሎች፣ እ.ኤ.አ. በ2011 በፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ ላይ የተነሳው ሕዝባዊ አመጽ መነሻ የሆነችውን ዴራ መያዛቸው ተሰምቷል።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኝ እና የሶርያን ግጭት የሚከታተል ተቋም እንደዘገበው "የአካባቢው አንጃዎች" ከመንግሥት ኃይሎች ጋር "ከባድ ጦርነት" ካደረጉ በኋላ ብዙ ወታደራዊ ቦታዎችን መቆጣጠር ችለዋል።
የሮይተርስ የዜና ወኪል የአማፂያን ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው የአገሪቱ ሠራዊት ለቅቆ እንዲወጣ እና ወታደራዊ ባለስልጣናት 100 ኪሜ ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ ዋና ከተማዋ ደማስቆ እንዲሸሹ መንገድ እንዲከፈትላቸው ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በሰሜን ሶሪያ የሚገኙ አማፂያን የሆምስ ከተማ አቅራብያ ደርሰናል እያሉ ቢሆንም ቢቢሲ እነዚህን ዘገባዎች ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።
አርብ ዕለት መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገው የሶሪያ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጅት እንዳስታወቀው ከሆነ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የሚንቀሳቀሱ አማፂያን የዴራ ክልልን ከ90% በላይ የሚቆጣጠሩ ሲሆን፣ የመንግሥት ኃይሎች እጅ የሚገኘው የሳናማይን አካባቢ ብቻ ነው ብሏል።
ዴራ ከተማ ስልታዊ እና ትዕምርታዊ ጠቀሜታ አላት።
የአውራጃ ዋና ከተማ መሆኗ ብቻ ሳይሆን ዮርዳኖስ ድንበር አቅራብያ ከሚገኙ ከተሞች መካከል አንዷ ናት። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በአውሮፓውያኑ 2011 ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድን የተቃወሙ ሰልፈኞች የተነሱባት ከተማ ናት።
ያንን ተከትሎም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው እና በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን የእርስ በርስ ጦርነት ተቀስቅሷል።
የዮርዳኖስ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር፣ በደቡብ ሶርያ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በመጥቀስ አገራቸው በአካባቢው የሚገኘውን ድንበር መዝጋቷን አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በኩርዲሽ የሚመሩ ኃይሎች በአገሪቱ ምሥራቃዊ አቅጣጫ የምትገኘውን እና የመንግሥት ዋና መቀመጫ የሆነችውን ዴር ኤዞር ከተማን መቆጣጠራቸውን ተናግረዋል።
በሰሜን የሚገኙ አማፂያን ከረዥም ዓመታት በኋላ የአገሪቱ ጦር ላይ ድንገታዊ ጥቃት ከፍተው ያለበትን ድክመት ካጋለጡ እንዲሁም ቁልፍ ከተሞችን መቆጣጠር ከጀመሩ አንድ ሳምንት አልፏቸዋል።
እንደ የተባበሩት መንግጅታት ድርጅት መረጃ ከሆነ በአማፂያኑ ጥቃት እስካሁን በትንሹ 370,000 ሰዎች ተፈናቅለዋል ተብሎ ይገመታል።
አክሎም ጦርነቱ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በሲቪሊያን ላይ እየደረሰ ያለውን አስከፊ ሁኔታ እያባባሰው ነው ብሏል።
አንዳንድ ንፁኃን ዜጎች ጦርነት በሚካሄድባቸው ስፍራዎች ውስጥ የሚገኙ በመሆኑ እስካሁን ድረስ ደህንነቱ ወደተጠበቀ አካባቢ ማዘዋወር አልተቻለም።
ባለፈው ሳምንት አማፂያን ጥቃት ከከፈቱ በኋላ በመላ አገሪቱ ከ820 በላይ ሰዎች፣ 111 ሲቪሊያንን ጨምሮ መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ገልጸዋል።
አማፂያኑ ሐሙስ ዕለት በሆምስ ሰሜናዊ ክፍል የምትገኘውን ሃማ ከተማን የያዙ ሲሆን ይህም ባለፈው ሳምንት አሌፖን መቆጣጠር ለተሳናቸው ፕሬዚደንት አሳድ ሁለተኛው ትልቅ ሽንፈት ሆኖ ተመዝግቧል።
የእስላማዊው ታጣቂ ቡድን፣ ሃያት ታህሪር አል-ሻም (ኤችቲኤስ)፣ መሪ አቡ መሀመድ አል ጃውላኒ ለሆምስ ነዋሪዎች "ጊዜያችሁ ደርሷል" ሲሉ ተናግረዋል።
አማፅያኑ ወደ ደቡብ እየቀረቡ ሲሆን፣ ሆምስ ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ የምትገኝ ቀጣይ ማረፊያቸው ሆናለች።
ቢቢሲ አማፂያኑ ተቆጣጠርን ያሏቸውን አካባቢዎች ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ ማረጋገጥ ባይችልም መቀመጫውን እንግሊዝ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ግን አማፅያኑ በከተማዋ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀው ይገኛሉ ሲል ገልጿል።
የሩስያ ጦር አውሮፕላኖች የአማፂያኑን ግስጋሴ ለመቀነስ በአቅራቢያው የሚገኘውን ራስታን ድልድይን በቦምብ ደብድበዋል።
የሶሪያ ጦር ለቀናት ተዋግቶ ሃማ ከተማን ለቅቆ ከወጣ በኋላ ሆምስን መከላከል ይችል እንደሆነ ግልፅ አይደለም።
የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ዋና ከተማዋን ደማስቆን በሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ ካለችው እና የአላዊት እምብርት ጋር ከሚያገናኘው ስትራቴጂካዊ ከተማ ወታደሮቻቸው መውጣታቸውን አስተባብለዋል።
አላዊቶች የአሳድ ቤተሰብ መገኛ ሲሆኑ፣ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ የሺዓ ሙስሊሞች ናቸው።
ለአሳድ አገዛዝ ትልቅ የድጋፍ መሰረት ጥለው ለረጅም ጊዜ የቆዩት አላዊቶች ፕሬዚዳንቱ በስልጣን ላይ እንዲቆዩ ቁልፍ ናቸው።
አሳድ አማፂያኑን "ለመደምሰስ" ቃል የገቡ ሲሆን የምዕራባውያን ኃይሎች የቀጠናውን ካርታ ለመቀየር እየሞከሩ ነው ሲሉ ከስሰዋል።
ተንታኞች ግን የአሳድ ጦር ኃይሎች በዝቅተኛ ደሞዝ እና በመኮንኖች መካከል በተንሰራፋው ሙስና የተነሳ የውግያ ሞራላቸው ተንኮታኩቷል ይላሉ ።
ይኹን እንጂ በቅርቡ የመንግሥት የዜና ወኪል ሳና እንደዘገበው ለሠራዊቱ የ50% የደመወዝ ጭማሪ ተደርጓል።
የአገዛዙ ዋነኛ አጋር የሆኑት ሩሲያ እና ኢራን ለአሳድ ቀጣይነት ያለውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ ክሬምሊን በዩክሬን በሚያደርገው ጦርነት የተጠመደ ሲሆን፣ ኢራን ደግሞ እስራኤል በሊባኖስ ሔዝቦላህ ላይ በከፈተችው ዘመቻ ምክንያት ተዳክማለች።
የጦርነቱን መባባስ ተከትሎም ሞስኮ የሩሲያ ዜጎች አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ስትጠይቅ፣ አርብ ዕለት ደግሞ አሜሪካ ዜጎቿን "በደማስቆ በረራዎች እስካሉ ድረስ" ሶሪያን ለቅቀው እንዲወጡ መክራለች።
የሩስያ እና የኢራን ባለስልጣናት በሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ላይ ለመምከር በሳምንቱ መጨረሻ ከቱርክ አቻቸው ጋር ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ቱርክ በአገሪቱ የሚንቀሰቀሱ አንዳንድ አማፂ ቡድኖችን የምትደግፍ ሲሆን ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን ለወራት አሳድን ከተቃዋሚዎች ጋር ፖለቲካዊ መፍትሄ ላይ አንዲደርሱ ግፊት ሲያደርጉ ነበር።
ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን የአማፂያኑ የቅርብ ጊዜ ግስጋሴ እንደሚደግፉ ተናግረው አሳድ ጥሪዬን ቢቀበል ኖሮ ይህ አይከሰትም ነበር ሲሉ ተደምጠዋል።












