ኔዘርላንድስ በቅኝ ግዛት ወቅት የዘረፈችውን ቅርሶች ልትመልስ ነው

ኔዘርላንድስ በቅኝ ግዛት ወቅት ስትገዛቸው ከነበሩ አገራት የዘረፈችውን ሃብቶች ልትመልስ ነው።

ኔዘርላንድስ ለኢንዶኔዢያ እና ስሪ ላንካ ከምትመልሰው ውድ ሃብቶች መካከል በውድ ማዕድናት ያጌጠ ከነሐስ የተሠራ መድፍ ይገኝበታል።

የኔዘርላንድስ የባሕል ሚንስትር ጉናይ ኡስሉ “በመጀመሪያ ደረጃ ወደ ኔዘርላንድስ መምጣት ያልነበረባቸውን ዕቃዎች ስንመልስ ይህ ለመጀመሪያ ግዜ ነው” ብለዋል።

ኔዘርላንድስ የተዘረፉ ንብረቶችን እንደምትመልስ ይፋ የሆነው አገሪቱ በቅኝ ግዛት ተሳትፎዋ ይቅርታዋን እየገለጸች ባለችበት ወቅት ነው።

የአገሪቱ መንግሥትም በቅኝ ግዛት ወቅት የተዘረፉ ንብረቶች እንዲመለሱ በባለቤት አገር ጥያቄ ከቀረበለት እንዲመለስ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብለት ነበር።

ቅርሶቹ እንዲመለሱ ሲጠይቁ ከነበሩት አንዱ የተዘረፉ ቅርሶችን በተመለከት ጥናት እንዲያደርግ በአገሪቱ መንግሥት የተቋቋም ኮሚቴ ነው።

ኮሚቴው የደች መንግሥት ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ቅርሶቹን እንዲመልስ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የኔዘርላንድስ ንጉሥ አገራቸው በባሪያ ንግድ ላይ ለነበራት ተሳትፎ ይፋዊ ይቅርታቸውን አቅርበው ነበር።

ንጉሥ ዊሌም-አሌክሳንደር በኔዘርላንድ የባሪያ ንግድ የቆመበት 160ኛ ዓመት ሲዘከር ባደረጉት ንግግር የባሪያ ንግድን “እጅግ አስከፊ” ብለው ከገለጹ በኋላ ኔዘርላንድስ በባሪያ ንግድ ውስጥ ለነበራት ተሳትፎ በራሳቸው እና በአገሪቱ ስም ይቅርታ ጠይቀዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሌሎች ቅኝ ገዢ የነበሩ አገራት ከጥንት በፊት የተዘረፉ ንብረቶችን ለባለቤት አገራት እየመለሱ ይገኛሉ።

የእንግሊዝ እና የጀርመን ሙዚየሞች እአአ 1897 ላይ በእንግሊዝ መንግሥት ከናይጄሪያ የተዘረፉ የቤኒን ነሐሶች ተብለው የሚጠሩ ውድ ሃብቶችን ለምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር መልሰዋል።

የኔዘርላንድስ የባሕል ሚንስትሩ አገራቸው የተዘረፉ ቁሶችን ከመመለስ በተጨማሪ ከአገራቱ ጋር በትብብር ትሰራለች ብለዋል።

ለኢንዶኔዢያ ከሚመለሱት ቅርሶች መካከል እአአ1894 ላይ አገሪቱ ቤተ-መንግሥቶች ከአንዱ የተዘፉ በውድ ማዕድና የተዋቡ ቅርጻ ቅርሶች፣ ውድ ማዕድናት፣ ወርቅ እና ብር ይገኙበታል።

ስሪ ላንካ ደግሞ አምስተርዳም በሚገኘው ሪጅክሰ ሙዚየም ለዕይታ ተቀምጦ የሚገኘውን የ18ኛው ክፍለ ዘመን የነሐስ መድፍ ትቀበላለች።