እስራኤልን ‘የሚጻረር’ ደብዳቤ ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ ሶስት የህግ ተማሪዎች የስራ እድላቸውን አጡ

በሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ ለፍልስጥኤም የተደረገው የድጋፍ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ ለፍልስጥኤም የተደረገው የድጋፍ ሰልፍ

ፍልስጥኤምን በመደገፍ አሁን ለተከሰተው ቀውስ እስራኤል ተጠያቂ መሆኗን የሚገልጽ ደብዳቤ ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ ሶስት የሃርቫርድ እና ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የህግ ተማሪዎች የስራ እድላቸውን አጡ።

በደብዳቤውም ምክንያት አንድ ሊቀጥራቸው የነበረ ታዋቂ የህግ ኩባንያም የስራ እድሉን ነፍጓቸዋል ተብሏል።

ዴቪስ ፖልክ እና ዋርድዌል የተባለው ኩባንያ በደብዳቤው ላይ የሰፈሩት አመለካከቶች “ከድርጅታችን እሴቶች ጋር የሚቃረኑ ናቸው” ብሏል።

በደብዳቤው ላይ የፈረሙት የዩኒቨርስቲ ተማሪ አመራሮች “ከእንግዲህ በድርጅታችን ውስጥ ተቀባይነት የላቸውም” ሲል አክሏል።

ስማቸው ያልተጠቀሱት እነዚህ ተማሪዎች በስመ ጥሩዎቹ ሃርቫርድ እና ኮሎምቢያ የሚማሩ ናቸው ተብሏል።

ነገር ግን ኩባንያውን በሚያስተዳድረው ኔይል ባር የተላከው እና ቢቢሲ የተመለከተው ኢሜይል መሰረት ውሳኔውን ለመቀልበስ ሁኔታዎች እንዳሉ የሚያሳይ ነው።

ኩባንያው ሁለቱን ተማሪዎች እያነገጋረ እንደሆነና ተማሪዎቹ ሊያቀርቧቸው የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎችንም እየገመገመ መሆኑንም ያሳያል።

በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ግጭት በአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዘንድ ከፍተኛ መወዛገቢያ እየፈጠረ ባለበትም ወቅት ነው ድርጅቱ ማክሰኞ ዕለት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው።

ኩባንያው ወደ 1 ሺህ የሚጠጉ ጠበቆች ያሉት ሲሆን ዓመታዊ ገቢውም 1.7 ሚሊዮን ዶላር ነው።

የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች የፍልስጥኤም የድጋፍ ኮሚቴ እና ሌሎች ከሰላሳ በላይ የተማሪ ማህበራት ባወጡት መግለጫ

“ስምምነቱን የፈረምነው የተማሪ ድርጅቶች የእስራኤልን አገዛዝ ለሁሉም ቀውሶች እና ሁከቶች ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ እናደርጋለን” ሲሉም በመግለጫቸው አስፍረዋል።

በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ለፍልስጥኤም የተደረገው የድጋፍ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ለፍልስጥኤም የተደረገው የድጋፍ ሰልፍ

ይህም ተቃውሞ ከአንዳንድ ወገኖች ያስነሳ ሲሆን አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ ለጋሾች ገንዘብ መስጠት እንደሚያቆሙ በመግለጽ ያስፈራሩ ሲሆን በሃርቫርድ የሚገኘው የአይሁድ ማዕከልም ጸረ ሴማዊ ነው ሲል መግለጫውን አውግዞታል።

በኮሎምቢያ የሚገኙ 20 የተማሪዎች ህብረትም የፈረሙበት ደብዳቤ በተመሳሳይ “ለጦርነቱ እና ለደረሰው ጉዳት ኃላፊነቱ የእስራኤል ጽንፈኛ መንግሥት እና ሌሎች የምዕራባውያን መንግሥታት ነው ” የሚል መልዕክት አስፍሯል።

ከአስራ ሁለት ቀናት በፊት ሐማስ በወሰደው ያልተጠበቀ ወታደራዊ እርምጃ 1ሺህ 400 ሰዎች በእስራኤል ተገድለዋል።

የሐማስ ታጣቂዎች በጋዛ ሰርጥ በኩል ድንበር ተሻግረው ነበር በንጹሐን እና በወታደሮች ላይ ጥቃት የፈጸሙት።

እስራኤል ላለፉት አስራ ሁለት ቀናት ቀን ተሌት ጋዛን በቦምብ በመደብደብ ላይ የምትገኝ ሲሆን በዚህም ከ3 ሺህ ሰዎች በላይ ተገድለዋል።

እስራኤል ጋዛ ሰርጥን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ከበባ እንዲደረግ ያዘዘች ሲሆን፣ በጋዛ 'ኤሌክትሪክ፣ ምግብ፣ ነዳጅ አይኖርም ሲሉም የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ባለፈው ሳምንት ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል።

ጋዛ ሰርጥ ወደ 2.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ፍልስጥኤማውያን መኖሪያ ስትሆን፣ ለ16 ዓመታት ያህል የቆየ ከበባ ውስጥ ትገኛለች።