በስፔን በሚካሄድ ፌስቲቫል ላይ ሦስት ሰዎች በኮርማ ተወግተው ሞቱ

በምሥራቃዊ ስፔን ከኮርማ ፊት በሚደረገው ዓመታዊ የሩጫ ፌስቲቫል ላይ የተጎዱ ሦስት ሰዎች ሕይታቸው አለፈ።

በ24 ሰዓታት ውስጥ ሕይወታቸው ያለፉት ሦስቱ ሰዎች በቫሌንሺያ በተካሄደው ባህላዊውና ዝነኛ ፌስቲቫል ላይ የተሳተፉ ናቸው ተብሏል።

በተለይ በቫሌንሺያ ግዛት ተቃዋቂ በሆነው በዚህ ፌስቲቫል ላይ በርካታ ሰዎች በጠባብ መንገዶች ከተቆጡ ኮርማዎች ፊት ለፊት መሮጥን ያካትታል። በዚህ ዝግጅት ላይ በርካቶች በኮርማ እየተረጋገጡ እና በቀንድ እየተወጉ ለከፋ ጉዳት ይጋለጣሉ።

የእንስሳት መብት ተካራካሪዎች ይህ ከኮርማ ፊት የመሮጥ ፌስቲቫል ለሰዎችም ሆነ ለእንስሳቱ ከፍተኛ ጉዳትን እያስከተለ ነው በማለት እንዲቆም ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

እነዚህ የመብት ተከራካሪዎች ከዚህ ባህላዊ ዝግጅት ጋር በተያያዘ ባለፉት 8 ዓመታት በቫሌንሺያ ግዛት ውስጥ 8 ሰዎች ሞተዋል ይላሉ።

ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ሕይወታቸው ያለፈው ሦስቱ ሰዎች ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተካሄደ ሥነ-ሥርዓት ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው ተብሏል።

ከሟቾቹ መካከል አንዱ የሆነውን የ56 ዓመት ጎልማሳ የተቆጣው ኮርማ ከመሬት ወደ ሰማይ ካሽቀነጠረው በኋላ በደረሰበት ጉዳት፣ የጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ አጋጥሞት ለቀናት በሆስፒታል ቆይቶ ሕይወቱ አልፏል።

ሜሊያና በምትባለው እና ሰሜን ቫሌንሺያ ከተማ በነበረው ፌስቲቫል ላይ በኮርማው ሹል ቀንድ ሳምባው ከተወጋ በኋላ ሕይወቱ ያለፈው የ50 ዓመት ጎልማሳም ከሟቾች መካከል አንዱ ነው።

የ64 ዓመት የፈረንሳይ ዜጋ ከሟቾቹ መካከል አንዱ መሆኑም ተገልጿል።

የሜሊያና ከተማ ከንቲባ ሰዎች አላስፈላጊ አደጋዎችን በራሳቸው ላይ እየደቀኑ ነው ብለዋል።

በስፔን ዝነኛ የሆነው ይህ ከኮርማ ፊት የመሮጥ ፌስቲቫል ዘንድሮ ብቻ 35 ሰዎችን ለጉዳት ዳርጓል። ይህ ፌስቲቫል ዘንድሮ የተካሄደው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ከተቋረጠ በኋላ ነው።

ፓክማ የተባለ የስፔን የእንስሳት መብት ተቆርቋሪ፤ አዘጋጆች ይህን ፌስቲቫል ከማስተባበር እንዲቆጠረቡ ሲጠይቅ ቆይቷል። የመብት ተቆርቋሪው ፌስቲቫሎቹ በእንስሳቱ፣ በተሳታፊዎች እና በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት እያስከተሉ ናቸው ይላሉ።

በሌላ በኩል እነዚህ ከኮርማ ፊት የሚደረጉ ሩጫዎች በተለይ ለቫሌንሺያ ግዛት ምጣኔ ሃብታዊ ትሩፋት ይዞ እንደሚመጣ ይነገራል።

እአአ 2019 ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እነዚህ ፌስቲቫሎች በቫሌንሺያ ግዛት ብቻ 3 ሺህ የሥራ ዕድሎችን መፈጥራቸውን እና 300 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ ማስገኘታቸውን አመልክቷል።