ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ-አፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ሊካሄድ ነው
የአሜሪካ- አፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በመጪው ታኅሣሥ ወር በዋሽንግተን ዲሲ እንደሚካሄድ ዋይት ሐውስ አስታወቀ።
የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት፣ ዋይት ሃውስ ትናንት ሐምሌ 13/2014 ዓ.ም. በድረ-ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ ከታኅሣሥ 04 አስከ ታኅሣሥ 06/2015 ዓ.ም ለሦስት ቀናት የሚካሄደውን የመሪዎቹን ጉባኤ ለማስተናገድ በጉጉት እየጠበቁ እንደሆነ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን መናገራቸውን አስፍሯል።
የመሪዎቹ ጉባኤ አሜሪካ ለአፍሪካ ዘላቂ አጋርነት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ያሉት ጆ ባይደን፣ አገራቸው ከአህጉሪቷ ጋር ያላት ግንኙነት ጠቃሚነት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ትብብርንም ይጨምራል።
የመሪዎቹ ጉባኤ የአሜሪካንና የአፍሪካን የጋራ እሴቶች ማዕከል ባደረገ መልኩ የኢኮኖሚ ተሳትፎን በአዲስና በተሻለ ሁኔታ ለማጎልበት ይገነባል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ ጉባኤውን አስመልክቶ በሰፈረው መግለጫ።
ጉባኤው አሜሪካ እና አፍሪካ ለዲሞክራሲ እና ለሰብዓዊ መብቶች ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደሚያጠናክርም ተገልጿል።
በተጨማሪም በዓለም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያደረሰው የኮቪድ- 19 ወረርሽኝንም ሆነ አዲስ የሚከሰቱ ወረርሽኞች በአገራቱ ላይ የሚያስከትሉትን ጫና መቀነስን በተመለከተ የመሪዎቹ ጉባኤ ይነጋገራል ተብሏል።
በዚህም ጉባኤው ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ጤናን ለማጠናከር በትብብር መስራት፣ የምግብ ዋስትናን ማጠናከር እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ምላሽ መስጠትንና የዲያስፖራውን ትስስር ለማጠናከር ከፍተኛ ሚናም እንደሚጫወት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በመግለጫቸው አስፍረዋል።
ከአፍሪካ መንግሥታት በተጨማሪ በአሜሪካ ካሉ ሲቪል ማኅበረሰብ፣ ከዳያስፖራው እንዲሁም ከግሉ ዘርፍ ጋር ለመስራት ፕሬዚዳንቱ ፍላጎት እንዳላቸው አስረድተዋል።
“የአሜሪካና የአፍሪካን የወደፊት ግንኙነት ለመገንባት በጋራ ራዕያችን ላይ አጠናክረን የምንሰራበትን መንገድ እጠብቃለሁ”ብለዋል።