ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሥራ ወኪሎች ‘ተታልለው’ ለሩሲያ እየተዋጉ ያሉት ሕንዳውያን
ሁለት ዓመት ባለፈው የዩክሬን እና የሩሲያ ጦርነት በርካታ ሕንዳውያን በሥራ ወኪሎች ተታልለው ለሩሲያ እየተዋጉ መሆኑን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች እየወጡ ነው።
በዩክሬን ለሩሲያ እየተዋጉ ካሉት ሕንዳውያን መካከል አንዱ በሚሳኤል ጥቃት መገደሉም ተነግሯል።
በሕንዷ ጉጅራት ግዛት የተወለደው ሄማል አሽዊንባሃይ ከሁለት ሳምንት በፊት በሚሳኤል ጥቃት መገደሉን የሂንዱ ጋዜጣ አስነብቧል።
የሄማል አባትን ቢቢሲ ከሁለት ሳምንት በፊት ባናገረበትም ወቅት ልጃቸውን ከሦስት ቀናት በፊት በስልክ አግኝውት እንደነበር ገልጸዋል።
የዩክሬንን ድንበር አልፎ 20 አስከ 22 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለ ስፍራ እንደተሰማራ እና የሞባይል ኔትወርክ ሲያገኝም በየጥቂት ቀናት ውስጥ ይደውልላቸውን እንደነበር ተናግረዋል።
የሄማልን ሞት ተከትሎም በሩሲያ በውጊያ ላይ ተሰማርተዋል የተባሉት ሕንዳውያን ቤተሰቦች ልጆቻቸው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የፌደራል መንግሥታቸውን እየተማጸኑ ይገኛሉ።
እነዚህ ተታልለው ወደ ውጊያ ተሰማርተዋል የተባሉት ሕንዳውያን ዕድሜያቸው ከ22 እስከ 31 ነው።
ሲመለመሉም “ሩሲያ ውስጥ በወታደራዊ ተቋም ረዳት” በሚል የተቀጠሩ ሲሆን፣ ወደ ዩክሬን የጦር ግንባሮች ሲላኩም “ሥልጠና” በሚል ምክንያት ነው ተብሏል።
በሩሲያ የሚገኙ ምንጮች በርካታ ሕንዳውያን የሩሲያን ጦር እንደተቀላቀሉ ጠቁመዋል። የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ምንጭን ዋቢ አድርጎ 'ዘ ሂንዱ' የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው ባለፈው ዓመት የተመለመሉት ሕንዳውያን ቁጥር ወደ 100 ይጠጋል።
የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ “አንዳንድ የሕንድ ዜጎች ለሩሲያ ጦር በድጋፍ ሰጪነት ሚና መመልመላቸውን” አምኗል።
“በሞስኮ የሚገኘው የሕንድ ኤምባሲ ሪፖርት የተደረጉለትን እያንዳንዱን ጉዳዮች ከሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር በመነጋገር እንዲሁም በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኩል የመጡትን ደግሞ በኒው ደልሂ ከሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ጋር በመወያየት ጥብቅ እርምጃዎች ተወስደዋል። በዚህም የተነሳ በርካታ ሕንዳውያን ከጦር ግንባሮች የግዳጅ እቀጠና ንዲወጡ ተደርጓል” ሲልም ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ አትቷል።
ሚኒስቴሩ አክሎም “ሁሉም ሕንዳውያን ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና ከዚህ ግጭት እንዲርቁ” አሳስቧል።
ተመልማዮቹ በወኪሎች ተታልለው እንዴት ወደ ጦር ግንባር እንደተላኩ ሲገልጹ የሚያሳይ ቪዲዮ ቤተሰቦቻቸውን አስደንግጧል።
ሁሉም በሚባል ሁኔታ እነዚህ ተዋጊዎች ወላጆቻቸው አቅመ ደካማ ናቸው። የባጃጅ ሾፌሮች፣ መንገድ ላይ ሻይ የሚሸጡ ወይም በሱቅ በደረቴ ሥራ ኑሯቸውን የሚገፉ ናቸው።
ተመልማዮቹ እና ቤተሰቦቻቸው እንደሚናገሩት እነዚህ ወኪሎች ለጥቂት ወራት በሩሲያ ሠራዊት ውስጥ ካገለገሉ በኋላ የሩሲያ ፓስፖርት እንደሚያገኙ ቃል ገብተውላቸዋል።
ለዚህም ደግሞ የሕንድ መገበያያ ገንዘብ የሆነው 300 ሺህ ሩፒ (3619) ዶላር መክፈል ነበረባቸው።
ወኪሎቹ ከሕንድ በተጨማሪ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኔፓል እና ስሪላንካ ይመለምላሉ። አንዳንድ ጊዜ የሚጠይቁትም ክፍያ እስከ 1.2 ሚሊዮን ሩፒ እንደሚደርስም ተገልጿል።
ቢቢሲ ለሩሲያ እየተዋጉ ያሉ ሕንዳውያን ቤተሰቦችን አነጋግሯል። ቤተሰቦቻቸው እንደሚሉት ከፍ ያለ ደመወዝ እንደሚጠብቃቸው ቃል የተገባላቸው ሲሆን፣ ምን ዓይነት አገልግሎት እንደሚሰጡ ግን አያውቁም ነበር ብለዋል።
በዩክሬን ተሰማርተው ያሉ ሕንዳውያንን ወንዶች ማንነት ቢቢሲ ለደኅንነታቸው ሲል አይገልጽም።
“የ28 ዓመት ልጄ ዱባይ ውስጥ በማሸጊያ ድርጅት ውስጥ ይሠራ ነበር። በሩሲያ ውስጥ ከ90 ሺህ እስከ 100 ሺህ ሩፒ ደመወዝ የሚያስገኝላቸው ሥራን የሚያስተዋውቅ ቪዲዮ ከሦስት ጓደኞቹ ጋር ሆነው በማኅበራዊ ሚዲያ ተመለከቱ።
“በዚያን ወቅት ያገኝ የነበረው ደመወዝ ከ35 - 40 ሺህ ሩፒ ነበር። ወኪሉ 300 ሺህ ሩፒ መክፈል እንዳለበት ስለነገረውም ተበድሮ ከፈለ። እባካችሁ ልጄ ወደ ቤቱ እንዲመለስ እርዱኝ” ሲሉም እንቁላል እና ሻይ መንገድ ዳር በመሸጥ የሚተዳደሩት አባት እያለቀሱ ለቢቢሲ ሂንዲ ተናግረዋል።
የዚህ ልጅ ታሪክ ከበርካታ የሕንድ ግዛት ተታልለው የተመለመሉ እና ለሩሲያ እየተዋጉ ያሉ ሕንዳውያን ታሪክ ጋር ተመሳሳይ ነው። ከእነዚህ ሁሉ አንድ ወጣት ብቻ ከሞስኮ አምልጦ ወደ ሕንድ መመለስ ችሏል።
አንድ ሕንዳዊ ከሞስኮ በጥር ወር መጨረሻ ላይ በተቀረጸ ቪዲዮ ላይ እንደሚናገረው “ባባቭሎግ በተሰኘ በአንድ ሕንዳዊ የሚተዳደር ዩቲዩብ ቻናል ነው ወደ ሩሲያ የመጣነው። 150 ሺህ ሩፒ የወር ደመወዝ እንደምናገኝም ቃል ገብቶልናል። ለጦር ሜዳ እየተመለመልን እንደሆነ አልተነገረንም” ያለ ሲሆን፣ ቢቢሲ ለዚህ የዩቲዩብ ቻናል ስለጉዳዩ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም።
ተታልለው ተመልምለዋል የተባሉት ሕንዳውያን የውጊያ ልምድ የላቸውም። የወታደራዊ መለዮ የለበሰ አንድ ሕንዳዊም እንዲሁ በማኅበራዊ ሚዲያ እንደተመለመለ ተናግሯል።
“ሞስኮ ከደረስን በኋላ በሩስኪ ቋንቋ ውል ፈርመን ሳናውቅ እንድንዋጋ ወደ ጦር ግንባር ተላክን። ተታለናል” በማለት የሚናገረው ይህ ወጣት ቀኝ እጁ እንደተጎዳ ያሳየ ሲሆን፣ ሌሎች ሁለት ሕንዳውያንም በጦርነቱ መቁሰላቸውን ሲናገርም ይደመጣል።
“እባካችሁ ከዚህ ቦታ አውጡን። ካለበለዚያ ጦርነቱ ወደተፋፋመበት ስፍራ ይልኩናል። ከባድ መሳሪያ የሚተፋው እሳት እንዲሁም ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) በየስፍራው እየወደቁ ነው። ውጊያ አናውቅም ። ወኪሎቹ አታለው በዚህ ቦታ ላይ ጥለውናል” በማለትም በቪዲዮው ላይ ተማጽኗል።
በሩሲያ እና በዩክሬን ድንበር ላይ ከምትገኘው ማሪዩፖል ቢቢሲ በስልክ ያናገረው ሕንዳዊ ተዋጊ ከእርሱ ጋር አንድ ሕንዳዊ፣ ዘጠኝ ከኔፓል የመጡ እና ኩባዊ መውጫ እንዳጡ ተናግሯል። በሥልጠና ወቅትም እግሩ መጎዳቱን ተናግሯል።
“የጦር አዛዡ ቀኝ እጅህን ተጠቅመህ ተኩስ፣ ግራህን ተጠቀም፣ ወደላይ ተኩስ፣ ወደታች ተኩስ” ይለኛል።
“በሕይወቴ ሽጉጥ ነክቼ አላውቅም። በጣም ቀዝቃዛ ነው። ሽጉጡን በግራ እጄ ይዤም ሳላውቀው እግሬ ላይ ተኮስኩኝ” ይላል።
ወንድሙ ተዋጊ የሆነ ግለሰብ በበኩሉ ሕንዳውያኑ “በሩሲያው ቅጥረኛ ቡድን ቫግነር ወይም በሩሲያ ጦር ውስጥ ይካተቱ አላውቅም። በዩክሬን ውስጥ ናቸው። በሦስት ወራት ውስጥም የሩሲያ ዜግነት እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸዋል” ብሏል።
ወደ ሩሲያ የሄደው ሻይክ መሐመድ ጣሂር የውጊያ ሥልጠና እንዲሁም በጦር ግንባር ሳይሰማራ ቀርቷል። በሩሲያ ቆይታውም “በአንድ የመኪና ባትሪ ፋብሪካ ውስጥ እሠራ ነበር” በማለት ከሳምንት በፊት ወደ ሕንድ የተመለሰው የ24 ዓመቱ ወጣት ተናግሯል።
ሕንዳውያኑ ተታልለለው ለጦርነት እየተመለመሉ እንደሆነ መነጋገሪያ የሆነው የሃይደራባድ ከተማ የፓርላማ አባል የሆኑት አሳዱዲን ኦዋይሲ ጥር አጋማሽ ላይ ስለጉዳዩ መናገራቸውን ተከትሎ ነው። ፖለቲከኛው ወጣቶቹን ወደ አገራቸው ለመመለስ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባም በመጠየቅ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤ ጽፈዋል።
የሕንድ ዋና ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ማሊካርጁን ካርጅ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት 100 ያህል ሕንዳውያን “በሩሲያ ጦር ውስጥ በረዳትነት ተመልምለዋል” ሲሉ ክስ አቅርበዋል።
“በአስንደጋጭ ሁኔታ አንዳንዶቹ ከሩሲያ ጋር ሆነው በጦር ግንባር ለመፋለም ተገደዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ ፓስፖርታቸው እና ሌሎች የጉዞ ሰነዶቻቸው ስለተወሰደባቸው ወደ አገራቸው መመለስ እንዳይችሉ ሆነዋል” ብለዋል።
የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ጅማሮ ላይ ጥቂት በጎ ፈቃደኞች ሕንዳውያን የዩክሬንን ጦር መቀላቀል ፈልገው እንደነበር ዘገባዎች ወጥተው ነበር። ነገር ግን ለሩሲያ ወግነው እየተፋለሙ ያሉ ሕንዳውያን መኖራቸው ሲነገር ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ለሩሲያ ወግኖ ሲፋለም የነበረ እና አገልግሎቱን የጨረሰ አንድ ሕንዳዊም ቢቢሲ አነጋግሯል። የሩሲያ ጦር ግልጽ እንደነበረ እና ከጦሩም ጋር የተፈራረመውን ውልም ለቢቢሲ አጋርቷል። ሆኖም ሩስኪ ቋንቋ የማያውቁ ሰዎች በወኪሎች እየታለሉ መሆናቸውን አክሏል።