ከዜሌንስኪ እና ትራምፕ የዋሺንግተን ውይይት የተወሰዱ ቁልፍ ጉዳዮች

የአውሮፓ አገር መሪዎች፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንሲ በዋይት ሐውስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የአውሮፓ መሪዎች ከፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ዜሌንሲ ጋር

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ ዕለት ለፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ዩናይትድ ስቴትስ የሩስያን ጦርነት ለማስቆም በሚደረገው ማንኛውም ስምምነት ለዩክሬን ደህንነት ዋስትና እንደምትሰጥ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቱ በዚህ ንግገራቸው ስለ እርዳታው ዓይነት እና መጠን ይፋ ያደረጉት ነገር የለም።

ትራምፕ ይህን ቃል የገቡት አርብ ዕለት በአላስካ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር መገናኘታቸውን ተከትሎ ዜሌንስኪን እና የአውሮፓ አጋሮቻቸውን ቡድን ባስተናገዱበት በዋይት ሐውስ በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ነው።

ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የዩክሬን ጦርነትን መቋጨት ላለመ ንግግር ነበር ሰኞ ዕለት በዋይት ሐውስ የተገኙት።

በዚህ ስብሰባ ላይ ለመካፈል በርካታ የአውሮፓ አገር መሪዎችም የተጓዙ ሲሆን፤ ንግግሩ የትራምፕ እና የፑቲን የአላስካ ጉባዔ ያለ ተኩስ አቁም ስምምነት በተጠናቀቀ በጥቂት ቀናት ውስጥ የተካሄደ ነው።

በትራምፕ ተስፈኛ ቃላት እና በአንዳንድ የአውሮፓ አገራት አዎንታዊ ግምገማዎች ቢደረጉም እስከ ሰኞ ምሽት ድረስ የደኅንነት ዋስትና ለመስጠትም ሆነ የሰላም ስምምነት ለማሰር መሬት የረገጠ ቁርጠኝነት አልታየም።

ንግግሩን ተከትሎ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው ለፑቲን ደውለው ከዜሌንስኪ ጋር ውይይት እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ገልፀዋል።

ስፍራው ወደፊት ይገለፃል የተባለው የሁለትዮሽ ውይይት ከተደረገ በኋላ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሚሳተፉበት የሦስትዮሽ ንግግር እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፑቲን አማካሪ ትራምፕ እና ፑቲን ለ40 ደቂቃ በስልክ መነጋገራቸውን ተናግረዋል።

ትራምፕ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ከደህንነት ጋር በተያያዘ ብዙ እርዳታ ይኖራል" ሲሉ የአውሮፓ አገራት ተሳታፊ ይሆናሉ ብለዋል።

"እነሱ እዚያ ስላሉ የመጀመርያው የመከላከያ መስመር ላይ ናቸው። ነገርግን እንረዳቸዋለን።

ዜሌንስኪ የተገባውን ቃል "ትልቅ እርምጃ" በማለት አሞካሽተው ዋስትናዎቹ "እስከ 10 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ በወረቀት ላይ ይሰፍራሉ" ብለዋል።

አክለውም ዩክሬን ወደ 90 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የአሜሪካን ጦር መሣርያ ለመግዛት እንደምትፈልግ ተናግረዋል

የአውሮፓ መሪዎች ለውይይቱ በጠረጴዛው ዙሪያ ከመቀመጣቸው አስቀድሞ ትራምፕ እና ኢማኑኤል ማክሮን በግል ሲነጋገሩ የተደመጠ ሲሆን፤ ፑቲንን በመጥቀስ "ስምምነት ማደረግ የሚፈልግ ይመስለኛል። ለእኔ ሲል ስምምነት የሚያደርግ ይመስለኛል" ሲሉ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናግረዋል።

ሩሲያ እአአ የካቲት 2022 ዩክሬን ላይ ሙሉ ለሙሉ ወረራ ከፈፀመች ወዲህ በሁለቱ ባላንጣ መሪዎች መካከል ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው የፊት ለፊት ንግግር ምን ያህል ቀጥተኛ ይሆናል የሚለው ወደፊት የሚታይ ጉዳይ ነው።

ለወራት ያህል ዜሌንሲኪ ፑቲንን ለማግኘት ሲገፉ የቆዩ ሲሆን፤ መሪዎቹ አለመገናኘታቸው ሩሲያ ለሰላም ስምምነት ፈቃደኛ አይደለችም በሚል ሲጠቀሙበት ቆይተዋል።

ሞስኮ የፑቲን እና ዜሌንስኪን ንግግር በተደጋጋሚ እንደማትቀበል ስትገልፅ ቆይታለች።

ጦርነቱን ለማስቆም ድርድር ከመደረጉ በፊት የተኩስ አቅም አስፈላጊነትን በተመለከተ ትራምፕ ውድቅ ያደረጉት ይመስላል።

"የሚያስፈልግ አይመስለኝም" ሲሉ ትራምፕ ስለ ተኩስ አቁም ስምምነቱ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት የዩክሬን ቁልፍ ፍላጎት የነበረ ሲሆን፤ አገሪቱ ከሩሲያ ጋር ለመነጋገር በስተመጨረሻም አስተማማኝ የሆነ ስምምነት ላይ ለመድረስ የተኩስ አቁም ስምምነት አስፈላጊ መሆኑን ስትወተውት ከርማለች።

የአውሮፓ መሪዎች ከትራምፕ በተቃራኒ የተኩስ አቁም ስምምነት ካልተደረገ በቀጣይ የሚደረግ የሰላም ስምምነት አይታሰብም በሚል ለተኩስ አቁም ግፊት እያደረጉ ናቸው።

ዜሌንስኪ ሲጠየቁ ከዚህ ቀደም ሲያደርጉት እንደነበረው የተኩስ አቁም ጥሪ ከማድረግ ተቆጥበዋል።

ትራምፕ ማንኛውም ጦርነቱን ለማስቆም በሚደረግ ስምምነት አሜሪካ ለዩክሬንን የደኅንነት ዋስትና እንደምትሰጥ ለዜሌንስኪ የእርዳታው ዝርዝር ሳይጠቅሱ ተናግረዋል።

አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ለመላክ ወጥና እንደሆነ በጋዜጠኞች ሲጠየቁም "አስተማማኝ ጥበቃ እንሰጣቸዋለን" ያሉት ትራምፕ ሀሳቡን ውድቅ አላደረጉትም።

የደኅንነት ዋስትናን በሚመለከት ትራምፕ አስረግጠው ሲናገሩ የመጀመሪያ ሲሆን፤ ይህም ከሩሲያ ጋር ለሚደረግ ስምምነት ወሳኝ እንደሚሆን ታምኖበታል።

ባለፈው ሳምንት በአላስካ በተደረገው ጉባኤ አሜሪካ ለዩክሬን የደኅንነት ዋስትና መስጠት የስምምነቱ አካል አድርጋ እንደምትሰጥ ፑቲን መቀበላቸውንም ገልፀዋል።

ዜሌንስኪ በሰጡት መግለጫ የደኅንነት ዋስትናው በአሜሪካ እና በዩክሬን መካከል የሚደረግ የ90 ቢሊዮን ዶላር የመሳሪያ ግዥን ያካትታል ብለዋል።

ለኪየቭ የሚሰጠው ዋስትና ዝርዝር ጉዳዮች በሚቀጥሉት 10 ቀናት ውስጥ ይሰራል ብለዋል።

ዜሌንስኪ ባለፈው የካቲት ወር በዋይት ሐውስ ኦቫል ኦፊስ ከአለባበሳቸው ጀምሮ ምስጋና ቢስ ተብለው ከፍ ዝቅ ተደርገው ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ወዳጅነቱ መሻሻሉን የሚያሳያ ምልክቶች ከፕሬዝዳንቱ ፊት ተነበዋል።

የአውሮፓ መሪዎችም ትራምፕ የውይይቱ አካል ስላደረጓቸው በምስጋና ሲያወድሷቸው ተደምጠዋል።