መንግሥት የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔን ወደ 17.5 በመቶ እንደማያሳድግ ገለጸ

የኢትዮጵያ መንግሥት ተጨማሪ እሴት ታክስን (ቫት) ወደ 17.5 በመቶ እንዲያሳድግ ቀረበለትን ምክረ ሀሳብ ተግባራዊ እንደማያደርግ ጠቆመ። መንግሥት በዚህ ዓመት አዋጁን ሲያሻሽል የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ 15 በመቶ ሆኖ እንዲቀጥል" መወሰኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ገልጿል።
የፌደራል መንግሥት ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ቫትን አሁን ካለበት "15 በመቶ ከፍ እንዲል ማድረግ ጫና" ሊፈጥር እንደሚችል የቀረበለትን ምክረ ሀሳብ በመቀበል መሆኑን ገልጿል።
የገንዘብ ሚኒስቴር የመንግሥትን ውሳኔ የሚያስረዳ ማብራሪያ ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም. ያወጣው የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ በ2.5 በመቶ ከፍ እንዲል የቀረበው ምክረ ሀሳብ በማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ከሆነ በኋላ ነው።
ይህ ምክረ ሀሳብ የቀረበው መንግሥት የሚሰበስበው ታክስ ከሀገሪቱ ጠቅላላ ምርት አንጻር ያለውን ምጣኔ በተመለከተ በተዘጋጀ ግምገማ ሰነድ ላይ ነበር።
ሰነዱ የዩናይት ኪንግደሙ የፖሊሲ ጥናት ተቋም "ኢንስቲትዩት ፎር ፊስካል ስተዲስ" ተመራማሪዎች ከገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ ፖሊሲ ዳይሬክቶሬት ጋር ያዘጋጁት ነው።
ኢትዮጵያ የምትሰበስበው ግብር ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ጋር ያለው ንጽጽር 7 በመቶ በመሆኑን ጠቀሰው ሰነዱ፤ ይህ ቁጥር ከሰሃራ በታች ባሉ አፍሪካ ሀገራት ካለው አማካይ ምጣኔ ያነሰ እንደሆነ በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል።
ሰነዱ ለዚህ በመፍትሔነት ካቀረባቸው ምክረ ሀሳቦች አንዱ ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነጻጻር "ዝቅተኛ" የሆነውን የኢትዮጵያ የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ ማሳደግ ነው። ከሰሃራ በታች ያሉ አፍሪካ ሀገራት የሚጥሉት አማካይ የቫት ምጣኔ 17.5 በመቶ መሆኑን ሰነዱ ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም አሁን ተጨማሪ እሴት ታክስ ካለበት 15 በመቶ ወደ 17.5 በመቶ እንዲያሳድግ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል። ይህንን ጭማሪ ማድረግ ግን የሚያስከትላቸው ጉዳቶች ሊኖሩ እንደሚችል ገልጿል።
ይህ ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ፤ መንግሥት ምክረ ሀሳቡን በመቀበል ቫትን በ2.5 በመቶ ሊጨምር ይችላል የሚሉ አስተያየቶች ሲንሸራሸሩ ቆይተዋል።
ይህንን ተከትሎ ዛሬ ማብራሪያ ያወጣው የገንዘብ ሚኒስቴር ጭማሪውን የማድረግ ዕቅድ እንደሌለ ጠቁሟል። የተደረገው ጥናት የኢትዮጵያ የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን እንዲሁም የቫት ምጣኔም አነስተኛ እንደሆነ ማረጋገጡን ጠቅሷል።
ባለፉት ዓመታት የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አንጻር ያለው ምጣኔ በፊት ከነበረበት "12 በመቶ በላይ" እየቀነሰ ለመምጣቱ "44 በመቶው" ድርሻ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንደሆነ ገልጿል።
ይህንን ተከትሎም "ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት መሠረታዊ የሚባል ማሻሻያ ሳይደረግበት" በቆየው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ላይ በዚህ ዓመት ማሻሻያ ተደርጉ ሥራ ላይ መዋሉን አስታውሷል።
አዋጁ ሲጸድቅ ከታክስ "ምጣኔ ውጪ ሌሎች ማሻሻያዎች" መካተታቸውን የገለጸው ገንዘብ ሚኒስቴር፤ ይህ የሆነው "መንግሥት የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ 15 በመቶ ሆኖ እንዲቀጥል በመወሰኑ" እንደሆነ አስረድቷል።
እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰውም "ምጣኔው አሁን ካለበት 15 በመቶ ከፍ እንዲል ማድረግ ጫናው በአግባቡ እየከፈሉ በሚገኙት ላይ እንዲባባስ በማድረግ የታክስ አስተዳደር ወይም የታክስ ተገዥነት ችግሩ ሊባባስ እንደሚችል ጥናቱ" በመጠቆሙ እንደሆነ ገልጿል።
የተጨማሪ እሴት ታክስ "ቀጥታ ካልሆኑ ታክሶች" ውስጥ እንደሚመደብ ያስረዳው ማብራሪያው፤ ከሌሎች የግብር ዓይነቶች አንጻር "ከፍተኛ ገቢ የማመንጨት አቅም" እንዳለው ጠቅሷል።
ነገር ግን ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶች "ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ያሳድራሉ፤ ተጨማሪ እሴት ታክስም በዚህ ላይ ተመሳሳይ ባህሪ አለው" ብሏል።
ይህ በመሆኑም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚጠቀሙባቸው "መሠረታዊ የሚባሉ እንደ የምግብ ሰብሎች እና ውጤታቸው" እንዲሁም "መሠረታዊ አገልግሎቶች" ከዚህ ግብር "ነጻ እንዲሆኑ" መደረጉን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።
ከዚህ በፊት ይህ ግብር ይጣልባቸው የነበሩት "የምግብ ማበልጸጊያ ቫይታሚኖች እና ያልበሰሉ ወይም ያልተዘጋጁ አትክልቶችም" ነጻ መደረጋቸውን አስታውሷል።















