የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች መነሻ ደመወዝ ወደ 11,500 ብር ከፍ ተደረገ

የፎቶው ባለመብት, Addis Ababa University
የፌደራል መንግሥት ከአንድ ዓመት በኋላ በድጋሚ ይፋ ባደረገው ደመወዝ ማሻሻያ 6,900 ብር የነበረው የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች መነሻ ደመወዝ ወደ 11,500 ብር ከፍ አለ።
በአዲሱ ማሻሻያ፤ ዝቅተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ላይ የ1,240 ብር ጭማሪ የተደረገ ሲሆን፣ ከፍተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ደግሞ በ17,508 ብር እንዲያድግ ተደርጓል።
ከመጪው መስከረም 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የደመወዝ ጭማሪ ይፋ የተደረገው ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም. ነው።
ለዓመታት የደመወዝ ማሻያያ ሳያደርግ የቆየው መንግሥት፤ "የሠራተኞች የኑሮ ውድነት ጫና መደጎሚያ" ሲል የጠራውን ጭማሪ ይፋ ያደረገው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ ነበር።
ከጥቅምት 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ መሆን የጀመረው ይህ ማሻሻያ ትኩረት ያደረገው ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ሠራተኞች ላይ እንደሆነም ተገልጾ ነበር። በዚህ ማሻሻያ ወቅት 1,110 ብር የነበረው ዝቅተኛ ደመወዝ ወደ 4,760 ብር ከፍ ተደርጎ ነበር።
በዝቅተኛ ደመወዝ ላይ የተደረገው የ332 በመቶ ጭማሪ ነበር።
በዚህ ማሻሻያ አሠራር መሠረት የደመወዝ እርከኑ ከፍ እያለ በመጣ ቁጥር የሚደረገው ጭማሪ አነስተኛ ተደርጓል። 20,468 ብር የነበረው ከፍተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ የተደረገበት ጭማሪ 1,023 ብር ነበር።
ዛሬ ይፋ የተደረገው አዲሱ ማሻሻያ በአንጻሩ የበለጠ ጭማሪ ያደረገው ለከፍተኛ ተከፋዮች ነው። ከፍተኛው የመንግሥት ደመወዝ ከነበረበት 21,492 ብር ወደ 39,000 ብር እንዲደረግ መወሰኑን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መግለጫ ያስረዳል።
በከፍተኛው ደመወዝ ላይ የተደረገው የ11,500 ብር ጭማሪ፤ በደመወዝ እርከኑ መጨረሻ ላይ ያሉ ሠራተኞች ደመወዛቸው በ81.4 በመቶ መጨመሩን ያመለክታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ይህ ማሻሻያ በዝቅተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ላይ ያደረገው 26 በመቶ ጭማሪ ነው። 4,760 ብር የነበረው ዝቅተኛው የመንግሥት ደመወዝ ከፍ የተደረገው 6,000 ሺህ ብር ነው።
በባለፈው ማሻሻያ የ76.4 በመቶ ጭማሪ የተደረገበት የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች ዝቅተኛ ደመወዝ አሁን የ65.7 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። በአዲሱ ማሻሻያ መሠረት ባለ ዲግሪ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ከ6,940 ብር ወደ 11,500 ብር ከፍ ተደርጓል።
"ከሲቪል ሰርቪስ ውጭ በተለያዩ ዘርፎች የተሠማሩ" የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝም ማሻሻያ እንደሚደረግበት መግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መግለጫ እንደሚያስረዳው ማሻሻያው የተደረገው ሰራተኞች ከመንግስት የኢኮኖሚ ሪፎርም "ውጤቶች እና ትሩፋቶች"፤ "በተገቢው መጠን" ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ነው።
ሐምሌ 2016 ዓ.ም. ተግባራዊ መሆን የጀመረውን ሪፎርም ተከትሎ "አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች፣ የቢዝነስ አንቀሳቃሾች እና በግል ክፍለ ኢኮኖሚ የተሠማሩ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የገቢ ሁኔታ" እየጨመረ መምጣቱን መግለጫው ጠቅሷል።
"ነገር ግን የቋሚ ደመወዝተኞች፣ በተለይም የመንግሥት ሠራተኞች ገቢ በተገቢው መጠን ሊጨምር አልቻለም" ሲልም ጭማሪ ያስፈለገበትን ምክንያት ገልጿል።
በመንግሥት ሠራተኞች ላይ ያለውን የኑሮ ጫና "በአንድ ጊዜ በሚደረግ የደመወዝ ማሻሻያ ሊቀረፍ እንደማይችል" እንደሚገነዘብ የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ሌሎች ማሻሻያዎችን ተግባራዊ እንደሚሆኑ አስታውቋል።
"የመንግሥት ሠራተኛው ችግር በደመወዝ ማሻሻያ ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ በቀጣይ የቤት አቅርቦትን እና የጤና መድን ሽፋንን ጨምሮ የተለያዩ መፍትሔዎች ይወሰዳሉ" ብሏል።
ከአዲሱ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው ማሻሻያ ከ160 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት እንደሚጠይቅ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መግለጫ ላይ ሰፍሯል።
ለዚህ የደመወዝ ማሻሻያ ያስፈለገው ተጨማሪ በጀት፤ ያለፈው ማሻሻያ ከጠየቀው 91 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት በ69 ቢሊዮን ብር የሚበልጥ ነው።
የፌደራል መንግሥት የጥቅምት ወሩን የደመወዝ ማሻሻያ ተግባራዊ ያደረገው የ582 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት በማጽደቅ ነበር።
አዲሱን ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ተጨማሪ በጀት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርብ እንደሆነ ግን አልተገለጸም።















