ኬንያዊቷ አትሌት ፌዝ ኪፕዮጎን በ1500 ሜትር ለአራተኛ ጊዜ በማሸነፍ ታሪክ ሰራች

ፌዝ ኪፕዮጎን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፌዝ ኪፕዮጎን በቶኪዮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1500 ሜትር ለኬንያ ወርቅ አምጥታለች

ኬንያዊቷ አትሌት ፌዝ ኪፕዮጎን በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1500 ሜትር አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ ታሪክ ፃፈች።

የ31 ዓመቷ አትሌት በወንዶች ምድብ በ1500 ሜትር ተመሳሳይ አሸናፊነትን ከተቀዳጀው ሂቻም ኤል ጉርጂ ጋር ታሪክ ተጋርታለች።

ባለፈው ዓመት በኦሎምፒክ ተከታታይ ሦስት ወርቆችን ያሸነፈችው ኬንያዊቷ አትሌት፤ በዓለም አትሌቲክስ ሻሚፒዮና ሦስት ወርቆችንም አግኝታለች።

በጃፓን ቶኪዮ እየተካሄደ ባለው የዓለም አትሌቲክስ ሻሚፒዮና የ1500 ሜትር ውድድር ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ በመቆጣጠር በመጨረሻው ዙር ከተቀናቃኞቿ ተስፈንጥራ በመውጣት ታሪክ ሰርታለች።

የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነችው ፊዝ ኪፕዮጎን ባለፉት አምስት የዓለም የውድድር መድረኮች አይበገሬነቷን በማሳየት በርቀቱ ከአራት ዓመት በላይ ሽንፈት አላስተናገደችም።

በምድቡ አውስትራሊያዊቷ የኦሎምፕክ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ የነሀስ ሜዳሊያ ስታገኝ፤ ኬኒያዊቷ ዶርከስ ኢዊ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች።

ፌዝ ኪፕዮጎን 3 ደቂቃ ከ52.15 ሰከንድ በመግባት አሸናፊነቷን ዳግም ስታረጋግጥ ሁለተኛ ከወጣችው የአገሯ ልጅ ኢዊ ጋር የሦስት ሰከንድ ብቻ ልዩነት ነበራቸው።

"እግዚያብሔርን ማመስገን እፈልጋለሁ" ስትል ለቢቢሲ ስፖርት ተናግራለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"የዓለምን ክብረ ወሰን [በ2015 መጀመሪያ] ከሰበርኩ በኋላ የበላይነቴን ለማስጠበቅ ብቁ እንደነበርኩ አውቄ ነበር። ዛሬ ጠንካራ በመሆኔ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።

"ባለመገፋፋት እና መውደቅ በምቾት መሮጥ ፈልጌ ነበር፤ ምክንያቱም ሰዎች ሲወድቁ ሳይ ትንሽ ፈርቼ ነበር። ራሴን መሆን እና ውድድሬን መሮጥ ነው የፈለኩት" ብላለች።

ድካም ባላዛላቸው እጆቿ እና በፈገግታ በተሞላ ፊቷ ፌዝ ኪፕዮጎን ያለምንም ጥርጣሬ በዓለም መድረክ ስምንተኛዋን የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቃለች።

ይህን ደረጃ በተመሳሳይ የውድድር ዓይነት አራት የወርቅ ሜዳሊያ ካገኙት ከኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ እና ከጃማይካዊቷ የአጭር ርቀት ፈርጥ ሼሊ አን ፍሬዘር ፕራይስ ጋር ተስተካክላ እንድትቀመጣ አድርጓታል።

ፌዝ ኪፕዮጎን በአንድ ውድድር ሁለተኛዋን ወርቅ ለማግኘት ማጣሪያውን ካለፈች የፊታችን እሁድ በ5000 ሜትር ትወዳደራለች።

ከሁለት ዓመት በፊት በዓለም ሻምፒዮና በ1500 ሜትር እና በ5000 ሜትር በማሸነፍ በሁለት ርቀቶች ድል ያደረገች የመጀመሪያዋ ሴት ሆናለች።

ኪፕዮጎን ባለፉት ስምንት የዓለም አቀፍ ውድድሮች በ2019 በዶሃ የዓለም ሻሚፒዎን በሲፋን ሀሰን በመነጠቅ ሰባት ጊዜ ማሸነፍ ችላለች።

የማይነኩ ክብረ ወሰኖችን ለመሰባበር ብርቱ ፍላጎት ያላት እና እናት የሆነችው አትሌቷ በተለይ ሕፃናት እና ሴቶችን ለማነሳሳት ባለፈው ሰኔ ወር አንድ ማይልን ከአራት ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ለመርጥ ሙከራ አድርጋለች።

ምንም እንኳ ይህ ሙከራዋ ባይሳካላትም የግሏን ሰዓት በፍጥነት በማሻሻል በታሪክ ከፈጣን ሴቶች በአምስት ሰከንድ ፈጥና በመግባት አቅሟን አስመስክራለች።

ኬንያዊቷ አትሌት ልጅ እያለች ከትምህርት ቤት ወደ መንደሯ በባዶ እግሯ ትሮጥ የነበረ ሲሆን፤ የመጀመሪያዋን ዓለም አቀፍ ውድድርም በባዶ እግሯ በመሮጥ ነው የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው።

በ1500 ሜትር ውድድር በእድሜ ትልቋ አትሌት ብትሆንም በጥንካሬ ቀጥላለች።