ከ55 ሚሊዮን ዶላር በላይ የወጣበት የዓለማችን ቢሊየነር ቤዞስ ሰርግ ለምን ተቃውሞ ገጠመው?

የአማዞን መስራች ጄፍ ቤዞስ እና ላውረን ሳንቼዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአማዞን መስራች ጄፍ ቤዞስ እና ላውረን ሳንቼዝ

የአማዞን መሥራች ጄፍ ቤዞስ እና እጮኛው ላውረን ሳንቼዝ በዚህ ሳምንት በጣሊያን ለሦስት ቀናት በሚቆይ ድል ባለ ሰርግ ሊጋቡ ነው።

ሰርጋቸው 'አረገደች ምድር' ተብሎ ሊዘፈንለት፣ ከዓይነት ዓይነቱ ሊበላ፣ መጠጥ እንደ ውሃ ፏፏቴ ሊፈስ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ተበጅቶለታል።

ግን ሰርጋቸው የአብርሃም እና የሳራ ይሁን የሚል ምርቃት ብቻ አላጀበውም። ባለ ቢሊዮን ዶላር ቱጃሩ ሰርጉን የሚጀምረው በውዝግብ ታጅቦ ነው።

ውዝግቡ ደግሞ በተቃውሞ ሠልፎች ጭምር የተደገፈ ነው።

ይህ ለቢሊየነሩ እና ለቀድሞዋ የፎክስ ቲቪ እና ኤቢሲ ጋዜጠኛ ሁለተኛ ጋብቻቸው ነው።

በቅርቡ የሚጋቡት ጥንዶች ለተወሰኑ ዓመታት አብረው የኖሩ ሲሆን፣ እአአ በግንቦት 2023 ደግሞ የቃል ኪዳን ቀለበት በማሰር እጮኛሞች መሆናቸውን በይፋ አውጀዋል።

ስለ ሰርጉ ምንም ዓይነት ዝርዝር መረጃ የለም። ነገር ግን በመጀመሪያው ዕቅድ መሠረት ቅዳሜ በጣልያን ቬኒስ መሀል ከተማ ታሪካዊ በሆነው ስኮላ ግራንዴ ዴላ ሜዜሪኮርዲያ ፍጻሜ እንደሚያገኝ ተሰምቷል።

ይኹን እንጂ ቢሊየነሩ ከፍተኛ ገንዘብ የተመነለት ይህ ሰርግ የሚፈጥረው ግርግር እና ሁከት ተቃውሞ ቀስቅሷል።

ስለዚህም የሰርጉ አጋፋሪዎች ቦታውን ለመለወጥ ተገድደዋል።

ጄፍ ቤዞስ እጁን እያውለበለበ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ራሱን ለቤዞስ የሚሆን ቦታ የለንም (No Space for Bezos) ብሎ የሚጠራው ቡድን ውስጥ የሚሳተፉት ቶማሶ ካቺያሪ "በዚህ በጣም እንኮራለን! እኛ ማንም አይደለንም። ገንዘብ የለንም፤ ምንም ነገር የለንም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"እኛ መደራጀት የጀመርን እና በዓለም ላይ ካሉት በጣም ሀብታም ሰዎች አንዱን፣ ሁሉም ቢሊየነሮችን፣ ከከተማ ማስወጣት የቻልን ዜጎች ነን።"

የከተማዋ ባለሥልጣናት እንደዚህ ዓይነት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቱጃር ጎብኚዎች ጠቃሚ የገቢ ምንጭ እንደሆኑ በመግለጽ ማኅበራዊ አንቂዎቹን አምርረው ተችተዋል።

የከተማው የኢኮኖሚ ልማት ምክር ቤት አባል ሲሞን ቬንቱሪኒ "እነዚህ ተቃዋሚዎች የቬኒስ ባለቤት እንደሆኑ አድርገው ነው ራሳቸውን የሚቆጥሩት፤ ግን አይደሉም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"እዚህ ማን እንደሚያገባ ማንም አይወስንም።"

ጄፍ ቤዞስ ለእጮኛው ላውረን ሳንቼዝን የቃል ኪዳን ቀለበት ያሰረው እአአ በግንቦት ወር 2023 ነበር

የፎቶው ባለመብት, Robert Smith / Patrick McMullan via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጄፍ ቤዞስ ለእጮኛው ላውረን ሳንቼዝን የቃል ኪዳን ቀለበት ያሰረው እአአ በግንቦት ወር 2023 ነበር

የ61 ዓመቱ ቤዞስ በዚህ ዓመት ፎርብስ መጽሔት የቱጃሮች ዝርዝር መሠረት ሀብቱ 227 ቢሊዮን ዶላር የተገመተ ሲሆን፣ የዓለማችን አራተኛ ሀብታም መሆኑም ተገልጿል።

ቤዞስ የአማዞን እና መንገደኞችን ወደ ጠፈር የሚያምላልሰው ብሎ ኦሪጅን ባለቤት ነው።

ጥንዶቹ ከቀድሞ ትዳራቸው በድምሩ ሰባት ልጆች አሏቸው።

ቤዞስ ከማኬንዚ ስኮት ጋር በነበረው የቀደመ ጋብቻ ሦስት ወንዶች ልጆች እና አንድ የማደጎ ሴት ልጅ አሉት።

ጥንዶቹ 25 ዓመታት አብረው ከቆዩ በኋላ በ2019 መፋታታቸውን በትዊተር የአሁኑ ኤክስ ይፋ አድርገዋል።

ፍቺያቸውን ሲያጠናቅቁም ባለቤቱ የድርሻዋ ነው የተባለውን 35 ቢሊየን ዶላር አግኝታለች።

35 ቢሊዮን ዶላር ድርሻዋን የተቀበለችው ማኬንዚ ከዓለማችን ሃብታም ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ገብታለች።

ይህ ብቻ ሳይሆን በዓለማችን ቁጥር አንድ ከሆነው የኢንተርኔት የችርቻሮ ግብይት ድርጅት አማዞን የአራት በመቶ ድርሻ አግኝታለች።

አዲሷ ሙሽራ የ55 ዓመቷ ሎረን ሳንቼዝ ሄሊኮፕተር የማብረር ፈቃድ ያላት ሲሆን፣ የብላክ ኦፕስ አቪዬሽን መሥራች ናት።

ይህም የመጀመሪያዋ በሴት ባለቤትነት የሚመራ እና የሚተዳደረው አየር ላይ የሚሠሩ ፊልሞች እና ፕሮዳክሽን ድርጅት እንደሆነ የብሉ ኦሪጅን ኤክስ አካውንት ያስረዳል።

አንድ ወንድ ልጅ ከቀድሞ የፍቅር አጋሯ ቶኒ ጎንዛሌዝ እና ሁለት ልጆች ከመጀመሪያው ባለቤቷ፣ የሚዲያ እና የመዝናኛ ሥራ አስፈፃሚ ፓትሪክ ዋይትሴል አሏት።

በትዳር ለ14 ዓመታት ቆይተዋል።

የማኅበራዊ አንቂዎች በቬኒስ የተለያዩ አካባቢዎች ፀረ ቤዞስ መፈክርን የያዙ ባነሮችን ሰቅለዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሰርጉን የሚቃወመው ማን ነው?

በታዋቂ ሰዎች የሚታጀበው ሰርግ ከበርካታ ቡድኖች ተቃውሞ ገጥሞታል።

በቬኒስ ቱሪዝምን የሚቃወሙ የአካባቢው ተወላጆች፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቾች እና ቤዞስ ለዶናልድ ትራምፕ የሚሰጠውን ድጋፍ የሚቃወሙ ይገኙበታል።

ሥነ ሥርዓቱ የታዋቂዋን ከተማ አንዳንድ ክፍሎች ሊያዘጋ ይችላል በሚል ስጋት በቬኒስ የሚገኙ አክቲቪስቶችም በቤዞስ ላይ ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎችን አድርገዋል።

አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች የሰርጉ ዝግጅት ሌላ የቬኒስ የማያባራ ብዝበዛ ምልክት አድርገው ይመለከቱታል።

ይህም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪዝም እና የሕዝብ ቁጥር መመናመን ጋር ተያይዞ የመጣ ነው።

በ1950 (እአአ) 175 ሺህ የነበረው የቬኒስ ነዋሪ ብዛት አሁን በተቃራኒው ከ49 ሺህ በታች ወርዷል።

ግሪንፒስ የተባለው የአካባቢ ጥበቃ ቡድን ቤዞስን የ"ልዩ መብት እና የብክለት ምልክት" ብሎታል።

"በቱጃሮች እና በቀሪዎቻችን መካከል ያለው ልዩነት እና የአየር ንብረት ተፅእኖ ማሳያ ነው" ሲልም አክሏል።

ሰኞ ዕለት የግሪንፒስ አክቲቪስቶች እና ራሱን 'ኤቭሪዋን ሄትስ ኤሎን' በማለት የሚጠራው ቡድን በቅዱስ ማርቆስ አደባባይ ቤዞስን በመቃወም ሠልፍ አካሄደዋል።

በተቃውሞ ሠልፉ ላይ "ለሰርግዎ ቬኒስን መከራየት ከቻሉ ከዚያ የበለጠ ግብር መክፈል ይችላሉ" የሚል መፈክር ይዘው ታይተዋል።

የሰርጉ ሥነ ሥርዓት ዛሬ [ሐሙስ] ምሽት በማዶና ዴል ኦርቶ እንደጀመር ጭምጭምታ ተሰምቷል።

ቦታው በደማቅ የምሽት ሕይወቱ የሚታወቅ እና የመካከለኛው ዘመን ቤተክርስቲያን መገኛ ነው።

የቬኒስ ከተማ አስተዳደር ለሳምንታት ተቃውሞ ያደረጉት የመብት ተሟጋቾችን ለመከላከል ረቡዕ ዐዕለት አካባቢውን እንዲዘጋ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የዶናልድ ትራምፕ ልጅ ኢቫንካ እና ባለቤቷ ጃሬድ ኩሽነር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የዶናልድ ትራምፕ ልጅ ኢቫንካ እና ባለቤቷ ጃሬድ ኩሽነር

በሰርጉ ላይ እነማን ይገኛሉ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቤዞስ እና የእጮኛውን ደስታ ደስታዬ ነው ያሉ ወደ 200 የሚጠጉ እንግዶች ተጋብዘዋል።

አንዳንዶቹ ለሰርጉ ዝግጅት ቀድመው የደረሱ ሲሆን፣ እንደ ፋሽን ዲዛይነር ዳያን ቮን ፉርስተንበርግ እንዲሁም የዶናልድ ትራምፕ ሴት ልጅ ኢቫንካ እና ባለቤቷ ጃሬድ ኩሽነር ቀድመው ከደረሱት መካከል ናቸው።

በግንቦት ወር በሳንቼዝ የፓሪስ በተዘጋጀው የላጤ ፓርቲ ላይ ከተገኙት እንግዶች መካከል ኪም ካርዳሺያን እና ክሪስ ጄነር፣ ድምጻዊት ኬቲ ፔሪ፣ ተዋናይ እና ፕሮዲዩሰር ኢቫ ሎንጎሪያ፣ ናታሻ ፖናዋላ እና የፎክስ ስፖርት አስተናጋጅ ቻሪሳ ቶምፕሰን ይገኙበታል።

ሰርጉ ላይ ሁሉም ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በዝግጅቱ ላይ ይገኛሉ ተብሎ ከተነገረላቸው ሌሎች ታዋቂ እንግዶች መካከል ኦፕራ ዊንፍሬይ፣ የሮክ ሙዚቀኛው ሚክ ጃገር እና ተዋናይ ሊዮናርዶ ዲካፕሪዮ ይገኙበታል።

እንደ ኢጣሊያ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ በአካባቢው የሚገኙ ሁሉም ቅንጡ ሆቴሎች እንዲሁም ጀልባዎች በሰርጉ ዝግጅት ተሳታፊዎች ተይዘዋል።

የግል አውሮፕላኖች የቬኒስ አየር ማረፊያን ያጨናነቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። የግል ጀልባዎች ወደቡን ይቆጣጠሩታል።

አምስት ሆቴሎች ሙሉ ለሙሉ የተያዙ ሲሆን፣ የቀድሞው የአሜሪካ የባሕር ኃይሎች ጥበቃ ለማድረግ መቀጠራቸውም ተሰምቷል።

ለሰርጉ እስከ 55.69 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚሆን የቬኒስ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።

እንዲህ ዓይነት በርካታ ዶላሮች የወጡበት ሰርግ በቬኒስ ሲካሄድ ይህ የጄፍ ቤዞስ ሰርግ የመጀመሪያው አይደለም።

እአአ በ2014 ተዋናይ ጆርጅ ክሎኒ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿን አማል አላሙዲንን ሲያገባ ሰርጉ እዚህ ቬኒስ ውስጥ ነበር የተከናወነው።

ከቤዞስ ሰርግ በተለየ፣ በወቅቱ በጆርጅ ክሉኑ የጋብቻ ድግስ ላይ ምንም ዓይነት ተቃውሞ እና ግርግር አልነበረም።