በቻይና ሁለት መንገደኞች አንዲት ጨቅላን የአውሮፕላን ሽንት ቤት ውስጥ መቆለፋቸው ቁጣ ቀሰቀሰ

የቻይናው ሁንያዎ አየር መንገድ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና ውስጥ ሁለት ቻይናዊያን ሴቶች እያለቀሰች ያስቸገረቻቸውን ጨቅላ የአውሮፕላን ሽንት ቤት ውስጥ መቆለፋቸው ቁጣ ቀስቅሷል።

ይህ ክስተት በቻይና ማኅበራዊ ሚድያዎች ላይ መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን ጨቅላዋን አንጠልጥላ ስትሄድ ቪዲዮውን የለጠፈችው ደግሞ ከሁለት ሴቶች አንዷ የሆነችው ጉ ቲንግቲንግ ናት።

ግለሰቧ ቪድዮውን ስትለጥፍ አውሮፕላን ውስጥ ያሉትን ሰዎች እንዳገዘች አድርጋ ቢሆንም ከማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ከፍተኛ ትችት ደርሶባታል።

አየር መንገዱ በሰጠው መግለጫ ሁለቱ ሴቶች ይህን ያደረጉት የሕፃኗ ሴት አያት “እንዲያስተምሯት” ፈቃድ ከሰጠቻቸው በኋላ ነው ብሏል።

ይህ የሆነው በአውሮፓውያኑ ነሐሤ 24 ከደቡብ ምዕራባዊቷ ጉዊያንግ ወደ ሻንግሀይ እየበረረ በነበረው የጁንያዎ አየር መንገድ በረራ ላይ ነው።

ከሴት አያቷ ጋር እየበረረች የነበረችው ሕፃን አውሮፕላኑ ሰማይ ላይ ሳለ ነው ማልቀስ የጀመረችው።

ይህ ከሆነ ከሁለት ቀናት በኋላ መግለጫ ያወጣው አየር መንገዱ ሁለት ሴቶች ሕፃኗን ወስደው ሽንት ቤት ውስጥ እንዲቆልፉባት ከአያት ፈቃድ ማግኘታቸውን ገልጿል።

የቻይና ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ቪድዮውን ያጋራችው አንደኛዋ ግለሰብ ሕፃኗ ማልቀስ ካላቆመች ሽንት ቤት ውስጥ ቆልፋባት እንደምትሄድ ስታስፈራራት ይታያል።

ምንም እንኳ አየር መንገዱ ስለሕፃኗ ምንም ዓይነት መረጃ ባያጋራም የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ግን የአንድ ዓመት ጨቅላ እንደሆነች ፅፈዋል።

ጉ ቪድዮውን ካጋራች በኋላ ነው ብዙዎች “ሀዘኔታ ያልፈጠረባት” እንዲሁም ሕፃናት “የምትበድል” ሲሉ ይነቅፏት የጀመረው።

ለዚህ ምላሽ የሰጠችው ጉ “ዳር ሆኜ ከመመልከት በላይ ተግባር ላይ የማተኩር ሰው ነኝ” ብላ በርካቶች የሕፃኗን ለቅሶ ሽሽት ወደ ኋላ ሄደው እንደነበር፤ አንዳንዶች ደግሞ ጆሮዋቸውን ሸፍነው እንደነበር ፅፋለች።

ግለሰቧ ከውዝግቡ በኋላ የማኅበራዊ ሚድያ ገፆቿን ማንም ሰው እንዳይጎበኘው አድርጋለች።

ጉዳዩን በተመለከተ ሐሳባቸውን የሰጡ የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች “ሕፃናት ስሜታቸውን መቆጣጠር አይችሉም። አንቺም ሕፃን ሳለሽ እንደዛ ነበርሽ” የሚል አስተያየት አስፍረዋል።

ሌሎች ደግሞ ሁለቱ ሴቶች ከሕፃኗ አያት ፈቃድ ስላገኙ ባደረጉት ነገር ትችት ሊቀርብባቸው አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።

ሕፃናት ሰው በሚበዛበት አካባቢ የሚያሳዩትን ባሕርይ በተለመከተ ቻይና ውስጥ ክርክር ተጀምሯል። አንዳንድ የባቡር ጣቢያዎች ለሕፃናት ብቻ የሚሆን ክፍል ማዘጋጀት ጀምረዋል።

ጎረቤት ሀገር ደቡብ ኮሪያ ደግሞ ሕፃናት የማይገቡባቸው በርካታ ምግብ ቤቶች፣ ሙዚየሞች እና ትያትሮች አሏት። ነገር ግን ሕግ አውጭዎች መንግሥትን እኒህን ቦታዎች መታገድ አለባቸው ምክንያቱም ሕፃናት እንደልባቸው የሚንቀሳቀሱበት ማኅበረሰብ ሊፈጠር ይገባል ሲሉ ይከራከራሉ።

የቱርክ እና ኔዘርላንድስ ንብረት የሆነው ኮሬንዶን አየር መንገድ እንዲሁም በሲንጋፖር የሚንቀሳቀሰው ስኩት አየር መንገድ ተጨማሪ ገንዘብ ለከፈሉ ተሳፋሪዎች ሕፃናት የማይደርሰቡት ወንበር ይሰጣል።