የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከወሲብ ወንጀለኛው ኤፕስቲን ጋር የተያያዙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰነዶችን አገኙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ባለሥልጣናት በሚቀጥሉት ቀናት እና ሳምንታት ውስጥ ይፋ የሚያደርጓቸው ከሕፃናት ወሲባዊ ጥቃት ፈጻሚው ጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር የተያያዙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰነዶችን ማግኘታቸውን ገለፁ።
የኤፍቢአይ እና የኒውዮርክ የፌዴራል አቃቤ ሕጎች ስለ ሰነዶቹ መገኘት ለፍትሕ ቢሮ አሳውቀዋል።
የፍትህ ቢሮ "ተጎጂዎችን ለመጠበቅ ሕጉ የሚጠይቀውን ሁሉ ለማድረግ ሌት ተቀን የሚሰሩ ጠበቆች አሉን፤ እናም ሰነዶቹን በተቻለ ፍጥነት እንለቃለን" ሲል ረቡዕ ዕለት ተናግሯል።
ቢሮው ሁሉም ሰነዶች ለሕዝብ ይፋ እስኪሆኑ ድረስ "ጥቂት ተጨማሪ ሳምንታት" ሊወስድ እንደሚችል ገልጿል።
የፍትህ ቢሮ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር እስከ ታህሳስ 19 ድረስ ሁሉንም የኤፕስቲን ፋይሎች ባለመልቀቁ ከፍተኛ ትችት ቀርቦበታል።
ቢሮው ግን "የፌዴራል ሕግን እና ፕሬዚዳንት ትራምፕ ፋይሎቹን ይፋ ለማድረግ የሰጡትን መመሪያ ሙሉ በሙሉ ማክበር እንቀጥላለን" ብሏል።
መግለጫው ኤፍቢአይ እና የፌደራል አቃቤ ሕጎች ተጨማሪ ሰነዶችን እንዴት እንዳገኙት በዝርዝር አላስቀመጠም።
ይህ ዜና የተሰማው የፍትህ ቢሮ በኤፕስቲን ላይ ካደረገው ምርመራ ጋር የተያያዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰነዶችን ይፋ ካደረገ በኋላ ነው። ከእነዚህ ሰነዶች መካከል የተወሰኑት እንዲሰረዙ ተደርጓል።
ኤፕስቲን ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕጻናት ለወሲብ ንግድ በማዘዋወር ክስ ችሎት ለመቅረብ እየጠበቀ በነበረበት ወቅት በኒውዮርክ እስር ቤት ራሱን ማጥፋቱ ይታወቃል።
የአሜሪካ የፍትህ ቢሮ ሰነዶቹን በተለያየ ጊዜ እያወጣ ሲሆን የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰነዶች አሁንም ይፋ እንደሚደረጉ ተናግረዋል።
ሰነዶቹ ለሕዝብ ይፋ መደረግ የጀመሩት ኮንግረስ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታዳጊዎችን በወሲብ ንግድ በማሰማራት የተፈረደበት ጄፍሪ ኤፕስቲን ሰነዶችን ይፋ እንዲያደርግ የሚያዝ ሕግ ከፈረሙ በኋላ ነው።
ሕጉ የተጎጂዎችን ማንነት በመጠበቅ ሁሉንም ሰነዶች ለሕዝብ እንዲያጋራ የሚያዝ ነው።
ብዙዎቹ ይፋ የሆኑት ሰነዶች፣ ቪዲዮዎችን፣ ፎቶዎችን፣ ኢሜይሎችን እና የምርመራ መዝገቦችን ጨምሮ ኤፍቢአይ ከኤፕስቲን ጋር አብረዋል ሲል የጠቀሳቸውን ግለሰቦች ስም የተቀነሰባቸው ናቸው።
የፍትህ ቢሮ ከዲሞክራቶችም ሆነ ከሪፐብሊካን ከሰነዶቹ ላይ በወጡ እና በተሰረዙ ማስረጃዎች የተነሳ ከፍተኛ ትችት ቀርቦበታል።
የኤፕስቲን ጉዳይን የያዘውን ኮሚቴ የሚመሩት የዲሞክራት አባል ተጨማሪ ሰነዶች ከተገኙ በኋላ በኤክስ ገጻቸው ላይ በጻፉት ጽሑፍ የፍትህ ቢሮ ሰነዶቹን "በሕገ-ወጥ መንገድ" ደብቋል ሲሉ ወንጅለውታል።
"በየቀኑ ውሸቶችን፣ የብቃት ማነስን፣ የጊዜ ገደቦችን አለማክበርን እና ሕገወጥ የማሻሻያ እርምጃዎችን እናያለን" ሲሉ የምክር ቤት አባል የሆኑት ሮበርት ጋርሲያ ተናግረዋል።
ኤፕስቴን ስመ ጥር ከሆኑ በርካታ ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበረው ሲሆን ግለሰቡ በ2019 እስር ቤት ውስጥ ሆኖ ፍርዱን እየተጠባበቀ ሳለ ራሱን አጥፍቷል።















