ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የስድስት ወሯን ጨቅላ የገደሉ የኬንያ ፖሊሶች ለፍርድ አለመቅረብ የፈጠረው ሐዘን
የስድስት ወሯ ጨቅላ ሰማንታ ፔንዶ በኬንያ ፖሊሶች ከተገደለች ሰባት ዓመታት አለፉ።
ከሰባት ዓመት በፊት የተደረገውን ብሔራዊ ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ ፖሊሶች በተለያዩ ስፍራዎች በወሰዷቸው አሰቃቂ እርምጃ መካከል በአንዱ ነው ህጻኗ የተገደለችው።
ወላጆቿ ጆሴፍ ኦሎ አባንጃ እና ስቴላ አቺየንግ በግድያዋ ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ ፖሊሶች ለፍርድ የመቅረብ ሂደት መዘግየቱ ከፍተኛ ሐዘን ውስጥ ከቷቸዋል።
"መቼም ቢሆን የማይቀረፍ ጠባሳ ነው" ስትል በደረሰባት ድብደባ የህጻን የራስ ቅሏ ተጎድቶ እና በውስጥ ደም መፍሰስ ሕይወቷ የተቀጠፈው የሰማንታ እናት ሌንሳ።
ህጻን ልጃቸውንን የገደሏት ፖሊሶች ዛሬ ነገ ለፍርድ ይቀርባሉ እየተባለ ይኸው ሰባት ዓመታት ተቆጥሯል።
ወላጆችም አሁንም በጨቅላነት ለተነጠቀችው ልጃቸው ፍትህን እየጠበቁ ነው።
ቤተሰቡ የሚኖረው በምዕራብ ኪሱሙ ነው። በአውሮፓውያኑ 2017 በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ የአገሪቱ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ዋነኛ የድጋፍ ይዞታ ናት ይህች ከተማ።
የምርጫውን ውጤት ተከትሎ ኪሱሙ ከፍተኛ ተቃውሞ አስተናግዳለች። ምርጫው አንዳንድ ጉድለቶች ታይተውበታል ተብሎም እንደገና መደገሙ ይታወሳል።
የቤተሰቡ ቤት ኒያሌንዳ በተሰኘች በተለምዶ ጨረቃ ቤቶች በሚባሉት ወይም ኢ-መደበኛ በሆነው ሰፈር ነው። በስፍራው የተነሳውን ተቃውሞ ለማስቆም ፖሊሶች ከተሰማሩባቸው ሰፈሮች አንዱ ነው።
በአንደኛ ዕኩለ ሌሊት ፖሊሶች የጎረቤቶቻቸው በሮችን ሰብረው ገብተው ነዋሪዎችን ሲደበድቡ ሰሙ።
ከዚያም ብዙም ሳይቆይ ፖሊሶች እነሱ ደጃፍ ላይ መጡ።
"በተደጋጋሚ አንኳኩ ከዚያም በሩን ይደበድቡት ጀመር። ነገር ግን ለመክፈት ፈቃደኛ አልነበርኩም" የሚለው የጨቅላዋ አባት ጆሴፍ ቤተሰቦቹን እንዲተውለት ፖሊሶቹን እየተማጸነ ነበር።
ይሄንን ተማጽኖ ያልሰሙት ፖሊሶች ቀዳዳ ሲያገኙ አስለቃሽ ጭስ የያዘች ቆርቆሮ ጣሉባቸው።
አንዷ ክፍል በጭስ ስትሞላ ቤተሰቦቹ ለመውጣት ተገደዱ።
ጆሴፍ ውጪ ላይ እንዲጋደም ታዘዘ እና ፖሊሶች ይደበድቡት ጀመር።
"ጭንቅላቴን ሊደበድቡኝ ሲሞክሩ እጄን ወደ ላይ አነሳሁ። እናም እጄ እስኪዝል ድረስ ይደበድቡኝ ጀመር" ይላል ጆሴፍ።
ባለቤቱ በአስለቃሽ ጭሱ ምክንያት ለመተንፈስ እየታገለች የነበረችውን ልጃቸውን ሳማንታን ከቤት ይዛ ወጣች።
"ልጄን እንዳቀፍኩኝ በዱላ ይደበድቡኝ ጀመር" ትላለች ስቴላ።
ቀጥሎ ጨቅላ ልጇ "ህመም እንደተሰማት በሚመስል መልኩ" ጭምድድ አድርጋ ስትይዛት ተሰማት።
ቀና አድርጋ ስታያትም ከአፏ አረፋ እየወጣ ነበር።
ልጄን ገደላችኋት እያለችም ስትጮህ ፖሊሶቹ ድብደባቸውን አቋረጡ።
ከዚያም አባትየው የመጀመሪያ እርዳታ እንዲያደርግ ታዘዘ። ህጻኗ በሕይወት የነበረች ቢሆንም ክፉኛ ተጎድታ ነበር።
ባልና ሚስቱ እንደሚናገሩት ፖሊሶቹ በፍጥነት ስፍራውን ለቀው ሲወጡ ጎረቤቶች ተረባርበው ጨቅላዋን ወደ ሆስፒታል ወሰዷት። ሆኖም ህጻኗ ለሦስት ቀናት ያህል በጽኑ ህሙማን ክፍል ከቆየች በኋላ ሕይወቷ አለፈ።
የህጻኗን ጨምሮ በሌሎች ግድያዎች፣ መድፈር እና ስቅይት ፈጽመዋል የተባሉ አስራ ሁለት ፖሊሶች ክስ ይመሠረትባቸዋል ተብሎ እየተጠበቀ ነበር።
ከተጎጂዎቹ ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት ዊልይስ ኦቲየኖ የፍርድ ሂደቱ የዘገየው ፖለቲካዊ ፍላጎት በመታጣቱ ነው ይላሉ።
በወቅቱ በድጋሚ በተካሄደው ምርጫ ኡሁሩ ኬንያታ የፕሬዚዳንትነቱን መንበር ሲያሸንፉ ተፎካካሪያቸው ራሳቸውን ከውድድሩ ማግለላቸው ይታወሳል። በወቅቱ ምክትላቸው የነበሩት እና በኋላ ፖለቲካዊ ጸብ ውስጥ የገቡት ዊልያም ሩቶ ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገው ምርጫ ማሸነፍ ችለዋል።
"መንግሥት ወንጀለኞችን ለፍርድ የማቅረብ ፍላጎት የለውም። ወንጀለኞችን ወደ ፍርድ የመውሰድ ኃላፊነት በተጎጂዎች፣ በመንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች እና በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ላይ ወድቋል። ይህንን ጥሰቶች የፈጸሙ ለፍርድ እንዲቀርብ ጫና እያደረግን ነው" ሲሉ ጠበቃው ዊልይስ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ለዚህም አንደኛው ተጠያቂ የሚያደርጉት የወቅቱን የሕዝብ ዐቃቤ ሕግ ዳይሬቶሬት (ዲፒፒ) ሲሆን፣ የ"ተከሳሾች ጠበቃ" ሆነዋል በማለት ወንጅለዋቸዋል።
ጠበቃው እንደሚሉት ባለፈው ጥቅምት እና ኅዳር ከዐቃቤ ሕግ ጋር በተደረሰ ስምምነት ተከሳሾቹ የጥፋተኝነት ምስክርነት ለመስጠት የነበሩ ሁለት ችሎቶች እንዲዘገዩ ለፍርድ ቤት ያመለከቱት "ተከሳሾቹ ሳይሆን ዐቃቤ ሕግ ነው" ይላሉ።
ሦስተኛው ችሎት ከቀናት በፊት እንዲደረግ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ዋነኛው ዳኛ መዛወራቸውን ተከትሎ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
የሕዝብ ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆንም "በቅርብ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። የህጻን ሰማንታ ፔንዶ ሞት ምርጫውን ተከትሎ በተፈጠረው አለመረጋጋት የነበረውን አሳዛኝ የፖሊስ ጭካኔ ማሳያ ነው" ሲል በኤክስ ገጹ አስፍሯል።
ነገር ግን በዚህ ጉዳይ እየተሳተፉ ያሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የፍርድ ሂደቱ መዘግየት አሳሳቢ ነው ይላሉ።
"ይህንን ጉዳይ ማየት የጀመረው የሕዝብ ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት (ዲፒፒ) ነው። ከበርካታ ዓመታት በፊትም ራሳቸው አናገሩን። ለፍርድ ሂደቱ ምስክሮች ለማሰባሰብ በነበረው ሂደትም በመሠረቱት ለተጎጂዎች ድጋፍ የሚሰጠውን ቡድን እንድንቀላቀል ጠየቁን" ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ኬንያ ኃላፊ ኢሩንጊ ሃውግተን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በመጀመሪያው ከተደረገው ምርመራ በኋላ የወቅቱ የሕዝብ ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ኃላፊ የነበሩት ኑረዲን ሐጂ የህጻን ሰማንታን ሞት በተመለከተ ማጣራት እንዲደረግ አዘዙ። በተካሄደው ማጣራትም ፖሊስ ጥፋተኛ ነው ሲሉ ውሳኔ ላይ ደረሱ።
በመቀጠልም በህጻኗ ላይ ብቻ ሳይሆን ፖሊስ በወቅቱ በወሰደው እርምጃ የደረሱ ጥሰቶች ላይም ምርመራ እንዲደረግ አዘዙ። ለዚህም ነጻ የሕገ መንግሥት የምርመራ አካላት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ እና የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር እንዲሳተፉ አደረጉ።
በተደረገው መጣራት "ግድያ፣ ማሰቃየት፣ መድፈር እና ሌሎች ፆታዊ ጥቃቶችን ጨምሮ ስልታዊ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። እነዚህም የከፉ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚያመለክቱ ናቸው" የሚል ድምዳሜ ላይ ተደረሰ።
ይህንንም ማጣራት ተከትሎ በአውሮፓውያኑ 2022 ኬንያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ ላይ ተመሥርታ ተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ ትመሠርታለች ተባለ።
ክስ ይመሠረትባቸዋል ከተባሉት መካከል ኃላፊነታቸው ያልተወጡ የበላይ መኮንኖች ነበሩበት።
ሆኖም በአውሮፓውያኑ 2023 የቀድሞው የሕዝብ ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክትሮት በአዲሱ ሬንሰን ኤም ኢንጎንጋ ተተኩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጉዳዩ ወደየትም ሊሄድ አልቻለም።
"ክስ ለመመሥረት ፈቃደኝነት ያለ አይመስለኝም" ይላሉ የአምነስቲው ኃላፊ ኢሩንጊ።
የፍርድ ሂደቱ መዘግየቱ ከቀጠለ በግል የዐቃቤ ሕግ ወይም ምሥራቅ አፍሪካ የፍትህ ፍርድ ቤት ወይም የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ለመሄድ እያጤኑ እንደሆነ የተጎጂዎቹ ጠበቃ ዊልይስ ይናገራሉ።
የኪሱሙ ገዢ እና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ፒተር አንያንጎ በበኩላቸው አንዳንዶችን ለመጠበቅ ሆን ብለው ይህ ክስ እንዳይመሠረት የሚያደርጉ ሰዎች ወይም አካላት ካሉ ጉዳዩን እንዲመለከቱት የአገሪቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ጠይቀዋል።
ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት መውሰድ አማራጭ እንደሆነ ፖለቲከኛው ይናገራሉ።
"የአካባቢው ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ማጓገተታቸውን ከቀጠሉ ለዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ለመጻፍ እንገደዳለን። ምክንያቱ የዘገየ ፍትህ የተነፈገ ያህል ነው" ብለዋል ፖለቲከኛው።
የሰማንታ ወላጆችም ይህንን ሃሳብ የሚደግፉ ሲሆን፣ ፍትህ ከሌለ ቁስላቸው መሻር አይችልም ይላሉ።
"በየትኛውም ሁኔታ ለልጄ ፍትህ ማግኘቴ አይቀርም" ይላል በባጃጅ አሽከርካሪነት የሚተዳደረው የ40 ዓመቱ ወላጅ አክሎም
"እሷ ለእኔ ሁሉም ነገሬ ነበረች። በእናቴ ስም ነበር የሰየምኳት። ያቺን ውዴን ነጠቁኝ" ብሏል።