የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ከሙስና ጋር በተያያዘ ክስ ሊመሰረትባቸው ይችላል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ “ከፋርማ ጌት” ቅሌት ጋር በተያያዘ ክስ ሊመስረትባቸው የሚችል ስጋት ከፊታቸው ተጋርጧል
ፕሬዝዳንቱ እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 በእርሻ መሬታቸው ላይ የተፈጸመውን የ4 ሚሊዮን ዶላር ዘረፋ ለመሸፋፈን ሰዎችን በማገት እና ጉቦ በመስጠት ጉዳዩን በዝምታ እንዲታለፍ ጥረዋል ተብለው ይከሰሳሉ።
ይህ ተዘረፈ የተባለው ገንዘብ ከሙስና ወይም ህጋዊ ያልሆነን ገንዘብ ህጋዊ ከማስመሰል ወንጀል ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል።
ገለልተኛ ከሆነ አካል ሾልኮ የወጣ አንድ ሪፖርት ራማፎዛ ስልጣናቸውን በመጠቀም ያልተገባ ድርጊት እንደፈጸሙ እና የጸረ ሙስና ህጉን ጥሰው ሊሆን እንደሚችል አመላክቷል።
እሳቸው ግን ይህንን ድርጊት አልፈጸምኩም ያሉ ሲሆን ተዘረፈ የተባለው ገንዘብ የተገኘው ከጎሽ ሽያጭ ነው ብለዋል።
ሾልኮ የወጣው ሪፖርት ለሀገሪቱ ፓርላማ ተላልፎ የሰጠ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት ጉዳዩን መርምሮ ራማፎዛ ላይ ክስ የመመሰረቱ ሂደት ይጀመር ወይም አይጀመር የሚለው ላይ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
ራማፎዛ ለፓርቲያቸው አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ወይም ኤኤንሲ እንደ አውሮፓውያኑ በ2024 ለሚካሄደው ምርጫ ለሁለተኛ ዙር ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር ይችላሉ ወይስ አይችሉም የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ጉባኤ ሊካሄድ ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ ሲቀረው ነው ከዚህ ጉዳይ ጋር ስማቸው የተነሳው።
ክስተቱ ራማፎዛ ለምርጫ ሲወዳደሩ ከጸረ ሙስና ጋር በተያያዘ ያላቸውን ዕቅድ ጥላሸት ሊቀባ የሚችል ነው ተብሏል።
የፓርቲያቸው ኤኤንሲ ስራ አስፈጻሚ ዛሬ ለምክክር የሚቀመጥ ሲሆን በዚህ ጉዳይ ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል።
የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ስለላ መስሪያ ቤት ሃላፊ አርተር ፋራሰር ፕሬዝዳንት ራማፎዛ እንደ አውሮፓውያኑ በ2022 በሰሜን ምስራቅ የደቡብ አፍሪካ ክፍል የሚገኘው ፓላ ፓላ የተሰኘው እርሻቸው ላይ የተፈጸመውን የ4 ሚሊዮን ዘረፋ በተመለከተ ለፖሊስ አቤቱታ ማቅረባቸውን ተከትሎ የፋርማ ጌት ቅሌት ለመጀመሪያ ጊዜ ህዝብ ጆሮ የገባው ባለፈው ሰኔ ወር ነበር።
ከቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸው የቀድሞ የስለላ መስሪያ ቤት ሃላፊ የተዘረፈው 4 ሚሊዮን ዶላር ህጋዊ ያልሆነን ገንዘብ ህጋዊ የማስመሰል ሂደት ወይም ከሙስና ጋር የተያያዘ ነው ያሉ ሲሆን ፕሬዝዳንቱ ጉዳዩ ይፋ እንደይወጣ እገታ እንዲፈጸም ወይም ጉቦ እንዲሰጥ አዘዋል ሲሉ ከሰዋቸዋል።
ይህንን ያህል ቁጥር ያለው ዶላር ይዞ መገኘት በሀገሪቱ የውጪ ምንዛሬን ለመቆጣጠር የወጣውን ህግ መጻረር ሊሆን ይችላል።
ራማፎዛ ስርቆት መኖሩን ያመኑ ቢሆንም የተሰረቀው ገንዘብ ከተባለው በታች ነው፣ ለመሸፋፈንም አልሞከርኩም ብለዋል።
ከጎሽ ሽያጭ በጥሬ ገንዘብ ከተከፈለው 580 ሺህ ዶላር ውስጥ የተወሰነው የእርሻ ቦታው ስር ካለ ሶፋ ስር ተሰርቋል ብለዋል።
“እንደተባለው ስርቆቱን የፈጸሙትን ‘አላደንኩም’ ወይም እንዲታደኑ ትእዛዝ አላስተላለፍኩም” ብለዋል ሪፖርቱን አውጥቶታል ለተባለው ገለልተኛ ተቋም በጽሁፍ ባስገቡት ምላሽ።
ሪፖርቱ የወጣው አካል ግን በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ ያለ ሲሆን ከስተቱን “እጅግ ከባድ ጉዳይ ነው” ሲል ገልጸታል።
ለጎሾቹ ግዢ ክፍያ ፈጸመ ስለተባለው ሰው የሚታወቀው መረጃ በቂ አይደለም የተባለ ሲሆን ከሁለት አመት ተኩል በኋላም እስካሁን የከፈለባቸውን እንስሳቶች እንዳልወሰደ ተገልጿል።
ሪፖርቱን ያወጣው አካል ይሄን ያህል ገንዘብ ሶፋ ስር ደብቆ ማስቀመጥም የተለመደ አይደለም ያለ ሲሆን ገንዘቡ ወደ ባንክ ሊገባም ይችል ሲል ገልጿል።
“ፕሬዝዳንቱ የተሰረቀው የውጪ ምንዛሬ ምንጩ ከየት እንደሆነ እና የገንዝብ ለውውጥን መነሻ በተመለከተ የሚናገሩበት አጋጣሚ ይፈጠራል ብለን እናስባለን” ብለዋል።
በተጨማሪም “ፕሬዝዳንቱ ጉዳዩ እንዲመረመር እና አንድን ተጠርጣሪ ለመያዝ ከናሚቢያ ፕሬዝዳንት እርዳታ ለማግኘት ስልጣናቸውን ያለአግባብ ተጠቅመዋል” ብሏል።
የናሚቢያ ፕሬዝዳንት ሃግ ጂንጎብ ጉዳዩ ላይ ምንም ተሳትፎ የለኝም ሲሉ ቀድም ሲል አስተባብለው ነበር።












