ቤተሰባቸው ጋቦንን ለ56 ዓመታት የገዛው አሊ ቦንጎ ማን ናቸው?

አሊ ቦንጎ ከጋቦን ፕሬዝዳንትነት በመፈንቅለ መንግሥት ተነስተው በቤታቸው የቁም እስረኛ ሆነዋል።

በሀብት ከናጠጠ ቤተሰብ የተወለዱ ‘ሞልቃቃ’ ናቸው የሚሏቸው አሉ። ጋቦንን መምራት ከቤተሰባቸው የወረሱት ‘መብት’ እንደሆነ የሚያምኑ ናቸው ተብለውም ይተቻሉ።

አንዳንዶች ግን ‘የለውጥ አራማጅ’ ናቸው ብለው ይከራከራሉ። የጋቦንን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ ያለሙና የአገሪቱን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ከፍ ለማድረግ የሠሩም ይሏቸዋል።

የቦንጎ ቤተሰብ ጋቦንን ለ56 ዓመታት መርቷል። የቀድሞ ዘፋኝ አሊ ቦንጎ አገሪቱን መምራት የጀመሩት አባታቸው ሲሞቱ ነው።

መፈንቅለ መንግሥቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ላሏት ጋቦን ጥያቄዎች ያጫረ ሆኗል።

ያሳለፍነው ቅዳሜ የተካሄደውን ምርጫ የአገሪቱ ጦር ውድቅ ካደረገ በኋላ ነው መፈንቅለ መንግሥቱ የተካሄደው።

ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ምርጫው ተጭበርብሯል ቢሉም አሊ ቦንጎ ምርጫውን እንዳሸነፉ ተገልጾ ነበር።

አሊ ቦንጎ ሲወለዱ የተሰጣቸው ስም አሌይን በርናንድ ቦንጎ ነበር። በአጎራባቿ ኮንጎ ብራዛቪል እአአ በ1959 ነው የተወለዱት።

በቢያፍራን ጦርነት ወቅት ከናይጄሪያ ደቡብ ምሥራቅ ግዛት በማደጎ እንተወሰዱ መላ ምቶች ቢኖሩም አሊ ቦንጎ ይህንን አስተባብለዋል።

አሊ ቦንጎ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳሉ አባታቸው ኦማር ቦንጎን መምራት ጀመሩ።

አባትየው ሥልጣን የጨበጡት እአአ በ1967 ነበር።

ስለ አሊ ቦንጎ መላ ምቶች መሰማት የጀመሩት ብዙም ሳይቆይ ነው።

“የተወለዱት ቤተ መንግሥት አይደለም። አባታቸው ፕሬዝዳንት ሲሆኑ ስምንት ዓመታቸው ነበር” ይላሉ ፈረንሳያዊው የታሪክ ተመራማሪና በጋቦን ፖለቲካ መጽሐፍ ያሳተሙት ፍራንኮስ ጋልሜ።

አሊ ቦንጎ የጋቦንን ቋንቋ አለመማራቸው ያስተቻቸዋል። ዘጠኝ ዓመት ሲሞላቸው የግል ትምህርት ቤት ገቡና ኋላ ላይ ሕግ አጠኑ።

ከጋቦን ውጭ መማራቸው ‘ቤተኛ አይደሉም’ ተብሎ እንዲታሰብ ማድረጉ ይነገራል።

እስልምናን ከተቀበሉ በኋላ እአአ በ1973 ስማቸውን ወደ አሊ ቀይረዋል። ከቤተሰባቸው እስልምናን የተቀበሉት እሳቸው ብቻ ናቸው።

እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ከሙስሊም አገራት ኢንቨስትመንት ለመሳብ ነው የሚሉ አሉ።

ዘፋኙ አሊ ቦንጎ

አሊ ቦንጎ ልጅ ሳሉ ሙዚቀኛ እንጂ ፖለቲከኛ አልነበሩም። እናታቸው ፔሸንስ ዳቦኒም ዘፋኝ ናቸው።

ከሙዚቃ በተጨማሪ እግር ኳስም ይወሳሉ።

በ1977 ‘ኤ ብራንድ ኒው ማን’ የተባለ አልበም ለቀዋል። ፕሮዲውሰሩ የጄምስ ብራውን ፕሮዲውሰር ቻርልስ ቦቢት ነበር።

አሊ ቦንጎ አልበም በለቀቁ አራተኛው ዓመት ላይ ነው ወደ ፖለቲካ የገቡት።

በአባታቸው ዘመን የመከላከያ ሚኒስትር ነበሩ። በዚህ ሥልጣን 10 ዓመት ቆይተዋል።

ከዚያ በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ። የአባታቸውን ሥልጣን ይይዛሉ ተብሎ ግን አልተጠበቀም ነበር።

“መጀመሪያ ላይ የጋቦን ሕዝብ አሊ ቦንጎን እንደ እጩ መሪ በቁም ነገር አልወሰደውም ነበር” ይላሉ የታሪክ ምሁሩ።

ኋላ ላይ ግን መሪ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ታሰበ።

አባታቸው በ2009 ነው የሞቱት። 42 በመቶ ድምጽ አግኝተው አሊ ቦንጎ ተመረጡ።

“ተመርጬ ነው እንጂ ሥልጣን ተሰጥቶኝ አይደለም” ነበር ያሉት።

ነገር ግን ሥልጣን ያገኙት በተገቢው መንገድ ስለመሆኑ ጥያቄዎች ቀጥለዋል።

በ2016 ምርጫ ዋነኛ ተቀናቃኝ የነበሩት ጂን ፒንግ ናቸው። ጂን የቀድሞ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ነበሩ። ከአሊ ቦንጎ እህት ሁለት ልጆች አሏቸው።

በፕሬዝዳንቱ የውድድር አካባቢ ድምጽ እንደተጭበረበረ ጂን ገልጸው ነበር። ሲቪል ማኅበራትም ተመሳሳይ አስተያየት ቢሰጡም ገዢው ፓርቲ ‘ጋቦኒዝ ዴሞክራቲክ ፓርቲ’ ክሱን አልተቀበለም።

የሙስና ክሶች

የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት የቦንጎ ቤተሰብ ጋቦንን አቆርቁዟታል ይላሉ።

ተፈጥሯዊ ሃብቷን በዝብዘዋል። ደኖቿን፣ ነዳጇን እና ሌላም እምቅ ሃብቷል ለግል ጥቅማቸው አውለዋል።

የሕዝብ ንብረት አውድመዋል። አገሪቱንም እንደ ግል ንብረታቸው ተጠቅመውባታል ተብለው ይከሰሳሉ።

አርጀንቲናዊው እግር ኳስ ተጫዋች ሊዮኔል ሜሲ በ2017 ጋቦንን መጎብኘቱ አነጋጋሪ ሆኗል።

የፈረንሳይ ፖሊስ የቦንጎን ቤተሰብ የሙስና ክሶች ለሰባት ዓመታት መርምሯል። በፈረንሳይ ዘጠኝ ቅንጡ መኪናዎችች ጨምሮ 39 ንብረቶች እንዳሏቸው ተደርሶበታል።

ክሱ በስተመጨረሻ ውድቅ ሆኗል። ለዚህም ምክንያት የሆነው የንብረት ብዝበዛ ስለመፈጸሙ በቂ ማስረጃ አለመገኘቱ ነው።

የቦንጎ ቤተሰብ ክሶቹን አስተባብሏል።

ቤተሰቡ ከፍተኛ ትስስሮች በመፍጠር ምዝበራ መፈጸሙን የተለያዩ ምንጮች ይፋ አድርገዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኝ ቲንክ ታንክ የሚሠራው ፖል ሜሊ እንደሚለው አሊ ቦንጎ “ብልህ ሰው ናቸው። ግባቸው ጋቦንን ወደ ቴክኖሎጂ መር አገር ማሳደግ ነው”።

የ2020 መረጃ እንደሚያሳየው ከነዳጅ የሚገኘው የአገር ውስጥ ገቢ 38.5% ሲሆን ከውጭ ንግድ ደግሞ 70.5% ገቢ ተገኝቷል።

ከነዳጅ የሚገኘው ገቢ ወደ አገር ውስጥ እድገት እንዲውል ባለማድረጋቸው አሊ ቦንጎ ይተቻሉ።

ሆኖም ግን ማዕድን በማውጣትና አካባቢን በማይጎዳ መንገድ በመሥራት እንደሚታወቁ ተንታኙ ፖል ሜሊ ይገልጻል።

የኮንጎ ጥቅጥቅ ደንን የሚጠብቅ ውሳኔ እንዳሳለፉና ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር ቀጣይነት ያላቸው ዕቅዶች እንዳወጡም ይናገራል።

በ2021 ጋቦን የካርበን ልቀትን በመቀነስ ክፍያ ያገኘች የመጀመሪያዋ የአፍሪካ አገር ሆናለች።

ሳዑዲ አረቢያ እና ኩዌትን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች በመጓዝ የአገራቸውን ምጣኔ ሀብት ለማሻሻል መሞከራቸው አሊ ቦንጎ ይነገርላቸዋል።

ከቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ጋርም ያላቸውን ግንኙነት አስቀጥለዋል።

በ2018 ሳዑዲ ጉብኝት እያደረጉ ሳለ ስትሮክ ያዛቸው። ለአንድ ዓመትም ከፖለቲካው ተገልለው ቆይተዋል።

በ2019 የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደርጎባቸው ከሽፏል። የሞከሩትም ታስረዋል።

አሊ ቦንጎ ካገገሙ በኋላ ገጽታቸውን እንደ አዲስ መገንባት ጀምረዋል።

ሆኖም ግን “ታማሚ ናቸው። መምራት አይችሉም” ከሚለው ሐሜት መላቀቅ አልቻሉም።

አሁን በመፈንቅለ መንግሥት በቤታቸው የቁም እስረኛ ሆነዋል።

በርካታ ጋቦናውያን ከ56 ዓመታት የቦንጎ ቤተሰብ አገዛዝ በኋላ ለውጥን እንደሚሹ አያጠራጥርም።