ኢራን በከፍተኛ የጦር መኮንኗ ላይ የተፈጸመውን ግድያ እበቀላለሁ አለች

የኢራን ኃያል የመከላከያ ሠራዊት የሆነው የእስላማዊው አብዮታዊ ዘብ ኮሎኔል ግድያን ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስዱ ዛቱ።

ፕሬዚደንቱ ይህን ያሉት ትናንት እሑድ በኢራን በኃያልነቱ ስሙ የሚጠራው የኢራን አብዮታዊ ዘብ (ሪቮሉሹነሪ ጋርድ) ከፍተኛ የጦር መኮንን የነበሩ ሰው ከተገደሉ በኋላ ነው።

ኮሎኔል ሳያድ ኾዳይ በዋና ከተማ ቴህራን በሚገኘው ቤታቸው በር ላይ መኪናቸው ውስጥ ተቀምጠው ሳሉ ነው የተገደሉት።

ገዳዮቹ ማንነታቸው ለጊዜው አልተለየም።

ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ የከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኑ ግድያን "የዓለም አቀፍ እብሪተኝነት እጆች" የፈጸሙት ነው በማለት አሜሪካና አጋሮቿን ከሰዋል።

የደኅንነት ባለሥልጣኖቻቸው የተፈጸመውን ወንጀል በጥልቀት እንዲመረምሩ ጥሪ ያቀረቡት ፕሬዝዳንቱ "የሰማዕታችንን ንጹህ ደም ባፈሰሱት ወንጀለኞች ላይ የበቀል እርምጃ መውሰዳችን አይቀርም" ብለዋል።

ኾኖም ሁለቱ ነፍሰ ገዳዮች በሞተር ሳይክል ተፈናጠው ወደ ኮሎኔሎ ከተጠጉ በኋላ አምስት ጥይቶችን አከታትለው ተኩሰውባቸው ተሰውረዋል።

እስካሁን ለግድያው ይህ ነው የሚባል ቡድን ኃላፊነቱን አልወሰደም።

የኢራን ፖሊስ ነፍሰ ገዳዮቹን በማደን ላይ ተሰማርቷል።

እኚህ ኮሎኔል መኪናቸው ውስጥ ሳሉ፣ የጥንቃቄ ቀበቷቸውን እንዳደረጉ፣ ተዝለፍልፈው እና ደም እየፈሰሳቸው የሚያሳዩ ምሥሎች ተሰራጭተዋል።

በኢራን ከሁለት ዓመት በፊት፣ አንድ ከፍተኛ የኑክሊየር ሳይንቲስት በተመሳሳይ ሁኔታ በቴህራን መገደላቸው ይታወሳል።

ኮሎኔሉ እጅግ ኃያል ጉልበት አለው የሚባለው የኢራን ሪቮሎሽነሪ ጋርድ ከፍተኛ መኮንን ነበሩ።

ይህ ልዩ ኃይል በብዛት ከኢራን ውጭ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በማቀነባበርና በማስፈጸም ይታወቃል።

አሜሪካ ይህን ወታደራዊ ክንፍ ሽብር በማቀነባበር ትከሰዋለች።

በመካከለኛው ምሥራቅ የብዙ ሽብር ጥቃቶች መነሻና አስፈጻሚ እንደሆነም ትናገራለች።

የኮሎኔሉን መገደል ተከትሎ የኢራን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኮሎኔሉ የተገደሉት "በአክራሪ ጠላቶቻችን" ነው ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ይህንን ሲሉ የአሜሪካንን እና የእስራኤል እጅ እንዳለበት እያመላከቱ ነው ይላሉ ተንታኞች።

ከቃል አቀባዩ ቀደም ብሎ ሌላ አንድ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን የኮሎኔሉ ገዳዮች እስራኤሎች ናቸው ሲሉ ተናግረው ነበር።

ይህ የጄኔራሉ ግድያ ለኢራን አዲስ አይደለም።

በፈረንጆቹ 2020 ጄኔራል ቃሲም ሱለይማኒ በኢራቅ ሳሉ በአሜሪካ የአየር ጥቃት መገደላቸው ይታወሳል። ቃሲም ሱለይማኒ የስመ ገናናው የቁዱስ ልዩ ኃይል ዋና አዛዥ ጄኔራል ነበሩ።

ቁዱስ ልዩ ኃይል ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ ወታደራዊ ግዳጅ የሚወጣ የኢራን ጦር ክንፍ ነው።

ያን ጊዜ የጄኔራሉን ግድያ ተከትሎ በዋሺንግተንና በቴህራን መካከል ከፍተኛ ወታደራዊና ፍጥጫ ተከስቶ ነበር።

በተመሳሳይ ዓመት ሙህሲን ፋኽሪዛድ የተባሉ ሥመ ጥር የኢራን ኑክሊየር ሳይንቲስት በቴህራን መገደላቸው ይታወሳል።

እኚህ ሳይንቲስት ኑክሊየር በማበልጸግ እጅግ ቁልፍ ሰው የነበሩ ሲሆን በየትኛውም ሥፍራ ሲንቀሳቀሱ ከፍተኛ አጀብ የሚከተላቸው ሰው ነበሩ።

ኢራን እኚህ ሳይንቲስቷ የተገደሉት በእስራኤል በርቀት መቆጣጠሪያ መሣሪያ አማካኝነት በረቀቀ መንገድ ስለመሆኑ በወቅቱ ይፋ አድርጋለች።