በምግብ እና የደንብ ልብስ እጥረት የሚፈተኑት የላይቤሪያ እስር ቤቶች

የፎቶው ባለመብት, GLENNA GORDON/AMNESTY INTERNATIONAL
በዚህ ወር መግቢያ ላይ በላይቤሪያ ዋና ማረሚያ ቤት ለታራሚዎች የሚቀርብ እንጥፍጣፊ ምግብ አለመኖሩ ታወቀ። ሁኔታው በሀገሪቱ እስር ቤቶች ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆዩ እና አስከፊ ሁኔታዎችን ያጋለጠ ነበር።
አቅርቦቱ እጥረት በሀገሪቱ የሚገኙ 15 ማረሚያ ቤቶችን ያዳረሰ ሲሆን ሁለቱን ደግሞ አዲስ እስረኞችን መቀበል የማይችሉበት ደረጃ ላይ አድርሷቸዋል።
ይህንን ችግር ለማቃለል የሀገር ውስጥ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጉዳዩ ከተሰማ ከሁለት ቀናት በኋላ ነበር እንቅስቃሴ የጀመሩት። ሆኖም ስር የሰደዱትን የላይቤሪያ እስር ቤቶች ችግር በቀላሉ ሊወገዱ የሚችሉ አይመስሉም።
የአትላንቲክ ውቅያኖስ አሻግሮ በተገነባው የሞንሮቪያ ማዕከላዊ እስር ቤት 1,400 ያህል ሰዎች ታስረው ይገኛሉ። እስር ቤቱ የተሰራው ግን ከ400 ሰው በታች ለመያዝ ነበር።
በእስር ቤቱ ያለው የምግብ እጥረት ታራሚዎቹን በከፍተኛ ብስጭት ውስጥ የከተተ ነው።
በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተከሰሰው እና ሶስት አመት በዚያ እስር ቤት ውስጥ የቆየ አንድ ታራሚ በምግብ እጦት የተሰማውን ብስጭት ገልጿል።
"መንግሥት በየቀኑ አንድ ሰሃን (ሩዝ) ነው የሚሰጠን። በቀን አንድ ጊዜ!" ሲል ምሬቱን ገልጿል።
ታራሚው ይህንን ሲናገር ቁጣና ብስጭት ፊታቸው ላይ የሚታይ ሌሎች ታራሚዎች አንገታቸውን እየነቀነቁ በአስተያየቱ ይስማማሉ።
የሞንሮቪያ ማዕከላዊ እስር ቤት ኃላፊ ቫርኒ ጂ ሌክ ሰዎችን በዚህ መልኩ አጭቆ ማስቀመጥ ብቻውን "የሰብዓዊ መብት ጥሰት" መሆኑን ያምናሉ።
ፍሮንት ፔጅ አፍሪካ ከተባለ የሀገር ውስጥ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስም ሃላፊው ያልተሟላ አገልግሎት እና የመሠረተ ልማት እጥረት ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል።
የምግብ እጥረቱ መከሰቱ ሲሰማ በሞንሮቪያ የሚኖረር አንድ ታዋቂ ባለሃብት ለከታማው እስር ቤት ምግብ አቅርቧል።

የፎቶው ባለመብት, GLENNA GORDON/AMNESTY INTERNATIONAL
"ጄቲ" በሚል ስሙ በስፋት የሚታወቀው ይህ ባለሃብት ለቢቢሲ ሲናገር እርዳታው "የእስረኞችን የለውጥ ሂደት ለመርዳት ያለመ ነው" ብሏል።
ከዚህም ባሻገር የሃይማኖታዊ መርሁ "ያላችሁን ምግብ ለሌሎች አካፍሉ ይላል" ሲል ገልጿል።
ይህንን የባለሃብቱን እንቅስቃሴ ተከትለው ፌሎውሺፕ ሊቤሪያ የተባለ እንቅስቃኤ ሩዝ እና ዘይት ለእስር ቤቶቹ አቅርቧል።
ችግሩ ግን የእስር ቤቱን አገልግሎት ለማስቀጠል በበጎ አድራጎት ላይ ተመርኩዞ መቀጠል አዳጋች ነው።
የብሔራዊ ማረሚያ ቤቶች መስሪያ ቤት ዳይሬክተሩ ሬቭ ሳይንለሰህሸ ክዋዳህ ለእስረኞች በቂ ምግብ አለማግኘት ከሚገጥሙት ፈተናዎች አንዱ ነው ሲሉ አረጋግጠዋል።
መንግሥት በየወሩ መቅረብ ያለበትን ገንዘብ መልቀቅ ባለመቻሉ የችግሮቹ ሁሉ መንስኤ ነው ብለዋል።
ለምሳሌ በፈረንጆቹ መስከረም ላይ ለምግብ ግዢ የታሰበው ገንዘብ የተገኘው ከፈረንጆቹ ገና በኋላ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግሯል።
በዚህ ምክንያት የእስር ቤቱ ተቆጣጣሪዎች እስረኞችን ለመመገብ "ከዚህም ከዚያም ገንዘብ ለመበደር" ተገደው ነበር።
ኃላፊው ከችግሮቹ ውስጥ አንዱ በብሔራዊ በጀት ውስጥ የእስር ቤቶችን ጉዳይ በተመለከተ ሲቀርብ "የእስር ቤት መተዳደሪያ" በሚል መቀረቡ ነው ይላሉ።
"[የእስር ቤቱ] በጀት የምግብ፣ ማደሪያ፣ መድሃኒት፣ ሕክምና፣ እድሳት እና የቁሳቁስ ግዢን ማካተት አለበት" ያሉት ኃላፊው፤ "አሁን እዚህ ሀገር ውስጥ ያሉን እስር ቤቶች በሙሉ ጊዜ ያለፈባቸው ናቸው። ይህ የሞንሮቪያ ማዕከላዊ እስር ቤትንም ይጨምራል። መጠገን አለባቸው" ሲሉ አክለዋል።
ለታራሚዎችም ሆነ ለማረሚያ ቤቶቹ የጥበቃ ሰራተኞች በቂ የህክምና አገልግሎት እና ተገቢ የደንብ ልብስ አለመኖሩንም አመልክቷል።
ለእስረኛ ለመጨረሻ ጊዜ የደንብ ልብስ የቀረበው ከ10 ዓመታት በፊት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አማካኝነት ነበር።
የማረሚያ ቤቶቹ ችግር ይህ ብቻ አይደለም። እስረኞችን ለማጀብ መኪናም ሆነ ነዳጅ የለም።
"እኔ ይህን በምናገርበት ሰዓት ታራሚዎችን በባለ ሶስት እግር ተሸከርካሪ ነው የምናመላልሰው" ይላሉ።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን ሲያጠናቅቅ ትቷቸው የሄዳቸው ተሽከርካሪዎች "ተቃጥለዋል ወይም በሌላ መልኩ ወድመዋል"።
የማረሚያ ቤቶቹ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከታቸው የፍትህ ሚኒስትሩ ፍራንክ ሙሳ ዲን ለቢቢሲ ሲናገሩ የችግሮቹን ስፋት መንግሥት እንደሚያወቀው እና በተደረገ ፍተሻ ጎልቶ የታየ ችግር ነው ብለዋል።
ነገር ግን ለችግሩ የአጭር ጊዜ መፍትሄ ያላቸው አይመስልም።
"ችግሮቹን ለመፍታት የሕግ አውጭው አስፈላጊውን ገንዘብና ግብዓት እንደሚመድብ እናምናለን" ብለዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2011 መንግሥት የማረሚያ ቤት አገልግሎቶችን ለማሻሻል የ10 ዓመት እቅድ ነድፎ ነበር። ሚኒስትሩ ይህ ዕቅድ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸው "ተግዳሮቶች አሉ" በማለት የታራሚዎች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን ተናግሯል።












