የማንችስተር ዩናይትዱ ግሪንዉድ በመድፈር ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የማንችስተር ዩናይትዱ እግር ኳስ ተጫዋች ሜሰን ግሪንዉድ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ በቀረበት የአስገድዶ መድፈር እና ጥቃት የመፈጸም ውንጀላ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ዋለ።
የማንችስተር ከተማ ፖሊስ ተጨዋቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የአካል ጥቃትን የደረሰባት አንዲት ሴት በማህበራዊ ሚዲያ ያጋራቻቸውን ምስሎች እና ቪዲዮዎች መነሻ ማድረጉን ገልጿል።
"በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሰው በአስገድዶ መድፈር እና ጥቃት በመፈጸም ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር መዋሉን ማረጋገጥ እንችላለን” ሲልም አስታውቋል።
ተጫዋቹ በእስር ላይ የሚገኝ ሲሆን ምራመራ እየተካሄደበት ነው።
ክለቡ ማንችስተር ዩናይትድ ቀደም ሲል ተጫዋቹ በቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት ላልተወሰነ ጊዜ ከልምምድም ሆነ ከግጥሚያ እንዳገደው ይፋ አድርጎ ነበር።
"የትኛውም አይነት ጥቃት” ተቀባይነት እንደሌለው የገለጸው ክለቡ፤ ጉዳዩን በማህበራዊ ሚዲያዎች በኩል ቢያውቀውም "እውነታው እስኪረጋገጥ" ድረስ ምንም አስተያየት አልሰጥም ብሏል።
ሜሰን ግሪንዉድ በማህበራዊ ሚዲያን ስሙ እየተነሳበት ስላለው ጉዳይ የሰጠው ምላሽ የለም።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 ለማንችስተር ዩናይትድ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው የ20 ዓመቱ ሜሰን ግሪንዉድ፤ በዩናይትድ አካዳሚ ደረጃ ያደገ ሲሆን ባለፈው ዓመት ነበር በክለቡ ለመጫወት የአራት አመት ውል የፈረመው።












