ጀርመን የጦር መሣሪያ ወደ ዩክሬን የማትልከው ለምንድን ነው?

የጀርመን ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የጀርመን ወታደሮች

ፑቲን ዩክሬንን ከዛሬ ነገ ይወራሉ እየተባለ ነው፡፡ ምዕራብ አገራት ከኮቪድ ወጣን ሲሉ አዲስ የፖለቲካ ትኩሳት ገጥሟቸዋል፡፡

የራሺያ ዩክሬን ላይ መዝመት አይቀሬ እንደሆነ ብዙ የደኅንነት ዘገባዎች እያረጋገጡ ነው፡፡

አይቀሬ እየተባለ ያለውን ራሺያ ወረራ ለመግታት እና ዩክሬንን ለመከላከል አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም መሳሪያዎችን ወደ ዩክሬን ልከዋል።

በዚህ ጭንቅ ውስጥ ግን የምዕራባውያኑ አጋር የሆነችው ኃያሏ አውሮፓዊት አገር ጀርመን ወደ ዩክሬን የጦር መሣሪያ ለመላክ አቅማምታለች፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ምዕራብ ወዳጅ አገራትን አስኮርፏል፡፡

ለመሆኑ ጀርመን ወደ ዩክሬን የጦር መሣሪያ መላክ ለምን ስጋት ላይ ጣላት?

ለዚህ ጠንካራ ፖለቲካዊና ታሪካዊ ምክንያቶች እንዳሉ ብዙዎች አይረዱም፡፡

ወደ ምሥራቅ በርሊን ጥቂት ተጉዞ አፈሩን ማረስ መልስ ይዞ ይመጣል፡፡ በዚያ ገበሬዎች ሲያርሱ ሞፈራቸው ብዙውን ጊዜ የሰው ራስ ቅል ይዞ ይወጣል፡፡ ይህ የ2ኛው የዓለም ጦርነት መጥፎ ትዝታ ነው፡፡

በ2ኛው የዓለም ጦርነት እጅግ ዘግናኙ ጦርነት የተደረገው በዚያ አካባቢ ነበር፡፡

በጸደይ 1945 እንደ አውሮጳውያኑ አቆጣጠር ሒትለር ዋሻ ውስጥ ተደብቆ የመጨረሻውን ደቂቃ ይጠባበቅ ነበር፡፡ የጀርመን ወታደሮች ግማሾቹ ሽሽት ይዘው ነበር፡፡ የተቀሩት ደግሞ በመከላከል ላይ ነበሩ፡፡

ውጊያው በዋናነት ከሶቭየት ወታደሮች ጋር ነበር፡፡ በዚያ ምሥራቅ በርሊን ስሎው ኮረብታ ይታያል፡፡ በዚያ የጀርመን ወታደሮች የሞት ሽረት ትግል ላይ ነበሩ፡፡

የራሺያ ሠራዊት ከባድ ጥቃት ሰነዘረ፡፡ ያቺ ኮረብታ አኬልዳማ ሆነች፡፡ ሶቭየቶች ጥቃት ሰንዝረው ድንበሩን ሰብረው ቢገቡም በዚያ ብቻ 30ሺህ የሩሲያ ወታደሮች አለቁ፡፡

የጀርመኖች እልቂ ስፍር ቁጥር አልነበረውም፡፡ ዛሬ ያ ቦታ ላይ ይህን አሰቃቂ ጦርነት የሚያስታውሱ መቃብሮችና መታሰቢያዎች አሉበት፡፡ ገበሬዎች ዛሬም ድረስ ሲያርሱ የሰው ራስ ቅል ያጋጥማቸዋል፡፡

ጀርመኖች ይህ የጦርነት ቁስል ጨርሶ አልጠገገላቸውም፡፡ በተለይ ከሩሲያ ጋር ምንም ዓይነት ጦርነት ውስጥ መግባትን አይሹም፡፡

ዛሬ ላይ የጀርመን ፖለቲከኞቹ ወደ ጦርነት የሚያስገቡ ሁኔታዎችን ለማስቀረት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ጀርመን ሰላም ፈጣሪ አገር እንድትሆን ነው የሚሹት፡፡ ይህ በጥብቅ የሚከተሉት ፖሊሲ ነው፡፡

አሁን በዚህ አሳሳቢ በሚባል ሰዓት ጀርመን ለዩክሬን የጦር መሣሪያ ለመላክ ያመነታችበት አንዱ ምክንያት ይኸው ነው፡፡

የሶቪዬት ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሶቪዬት ወታደሮች

የጀርመን ወታደሮች በጣም የግድ ካልሆነ እስከዛሬም ሰላም በማስከበር ተልእኮ እንጂ በሌላ ጦርነት ውሰጥ እጃቸውን አያስገቡም፡፡

ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በ90ዎቹ በባልካን እንዲሁም በቅርቡ በአፍጋኒስታንና ኢራቅ ካልሆነ ጀርመኖች ወደ ጦርነት አይዘምቱም፡፡

የሚገርመው ደግሞ ጀርመን ከአሜሪካና ሩሲያ ቀጥሎ የጦር መሣሪያን ወደ ውጭ አገር በመላክ የሚያህላት የለም፡፡ ያ ግን ንግድ ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡

መሣሪያ ሽያጩም ላይ ቢሆን ወደየት እንደሚሸጥ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ ጀርመን ገንዘብ ላቀረበ አገር ሁሉ መሣሪያ አታቀብልም፡፡

ናዚ በዩክሬንና ሩሲያ በመቶ ሺዎች ገድሏል፡፡ ያ ቁስል አልጠገገም፡፡

አሁን ወደ እነዚህ አገራት በተለይም ወደ ዩክሬን ጦር መሣሪያ መላክ ለጀርመን ቀላል ጉዳይ አልሆን ያለውም ለዚሁ ነው፡፡

መራሒተ መንግሥት አንጌላ መርከል በኦላፍ ሾልዝ ተተክተዋል፡፡

አንጌላ ግን የፑቲን ጥሩ ወዳጅ ነበሩ፡፡ ቢያንስ ይግባቡ ነበር፡፡ ቢያንስ ሁለቱም የጋራ የልጅትን ትዝታ ነበራቸው፡፡ ፑቲን ጀርመንኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ፡፡ ይህን ክህሎት ያዳበሩት በቀድሞ ምሥራቅ ጀርመን በመሥራታቸው ነው፡፡

አንጌላም የተወለዱት በሶሻሊስት ምሥራቅ ጀርመን ነው፡፡ ልጅነት አግባብቷቸው ነው መሰል ፑቲን ለብዙ የአውሮጳ መንግሥታት የዘጉትን ዲፕሎማሲ ለአንጌላ መርከል ብቻ ነበር ገርበብ የሚያደርጉት፡፡

ተተኪያቸው መራሒ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ወደ ኪያቭ የጦር መሣሪያ ለመላክ በፍጹም አልደፈሩም፡፡ ፓርቲያቸውም ይህን እንዲያደርጉ ድጋፍ አልሰጣቸውም፡፡ ይልቁንስ የሜዳ ላይ ጊዚያዊ ሆስፒታል መገንቢያ ገንዘብ ልከዋል፡፡ ይልቁንስ ጀርመን የዩክሬን ወታደሮች ሲቆስሉ አክማለሁ ብላለች፡፡ ይልቁንስ ለዩክሬን ወታደሮች ጦር መሣሪያ ሳይሆን ጥይት መከላከያ ቆብ (ሄልሜት) እልካለሁ ብላለች፡፡

ከዚሁ ሁሉ ውሳኔ ጀርባ ያለው ዋናው ምክንያት ታዲያ ፖለቲካዊና ታሪካዊ ነው፡፡ ጀርመን ከ2ኛ የዓለም ጦርነት ወዲህ ሁሉም የፖለቲካ አለመግባባቶች በንግግር መፈታት አለባቸው የሚል ጠንካራ የውጭ ፖሊሲ ቀረጻለች።

ጀርመንና ሩሲያ በንግድ በጣም የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ከንግድ ልውውጦቹ ሁሉ እጅግ ወሳኑ ኖርድስትሪም2 የተባለው የጋዝ ማስተላለፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ ሩሲያን እጅ ለመጠምዘዝ ይህን የጋዝ ማስተላለፊያ ፕሮጀክት ማጠፍ በቂ ነው የሚሉ ተንታኞች አሉ፡፡

ይህ የጋዝ ማስተላለፊያ ከሩሲያ ወደ አውሮጳ ይገባ የነበረን የጋዝ መጠን በሁለት እጥፍ ያሳድጋል የተባለለት ነው፡፡

መራሒ መንግሥት ሾልዝ ቢያንስ ወታደር ባይልኩ ይህን ፕሮጀክት እንዲያቋርጡ ግፊት እየበዛባቸው ነው፡፡

ይህንንም ለማድረግ አልደፈሩም፡፡ ምናልባት ይህን ማድረግ ፑቲንን ይበልጥ ሊያስቆጣ ይችላል ከሚል ፍርሃት የመነጨ ይመስላል፡፡

እንደተፈራው ፑቲን ዩክሬን ላይ ከዘመቱ ጀርመን እጇን አጣጥፋ ትመለከት ይሆን?