እውቁ የቴኒስ ተጫዎች ጆኮቪች ከአውስትራሊያ ተባረረ

የዓለማችን ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ኮኮብ ኖቫክ ጆኮቪች በአውስትራሊያ ለመቆየት ባደረገው የመጨረሻ ፍርድ ቤት ክርክር ተረትቶ አገሪቱን ለቆ እንዲወጣ ተደረገ።

ክትባት ለመቀበል አሻፈረኝ ያለው የሜዳ ቴኒስ ተጫዋቹ፤ የአገሪቱ መንግሥት "በጤና እና ባልተገባ ስነምግባር" ምክንያት ቪዛውን መሰረዙን ተከትሎ ጆኮቪች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ቢወስደውም ፍርድ ቤቱም ይግባኙን ውድቅ አርጎበታል።

በውሳኔው "በጣም ቅር ብሎኛል" ያለው ጆኮቪች ውሳኔው ተቀበሎ ወደ ዱባይ አቅንቷል።

አገሩ ሰርቢያ 'በአውስትራልያ ኦፕን' የቴኒስ ውድድር ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ያደረገችው ጥረትም ፍሬ አልባ ሆኗል።

የጆኮቪች ደጋፊዎች ከውድድሩ የመክፈቻ ጨዋታውን አንድ ቀን ቀደም ብሎ የተወሰነውን ውሳኔ ከችሎቱ ውጪ ሆነው በቁዘማ ተከታትለዋል።

ከደጋፊዎቹ መካከል አንዷ በውድድሩ ላይ የዚህ ዝነኛ ተጫዎች አለመኖር የእረፍት ጊዜዋን "ባዶ" እንደሚያደርግባት ተናግራለች።

የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን "ድንበሮቻችንን ለማጠናከር እና አውስትራሊያውያንን ለመጠበቅ የተደረገ ውሳኔ ነው" ሲሉ ውሳኔውን በአውንታ መቀበላቸው ገልጸዋል።

ሆኖም ጠቅላይ ሚንስትሩ እና አስተዳደራቸው የጆኮቪችን ጉዳያ የያዙበት መንገድ በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጪ እያስተቻቸው ነው።

የጆኮቪች ጉዳይ መነሻ የአውስትራሊያ ኢሚግሬሽን ሚኒስትር አሌክስ ሃውክ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ቪዛውን ከሰረዙ በኋላ ነው። ምክንያት ያሉት ደግሞ በአገሪቱ የፀረ-ክትባት እንቅስቃሴን ሊያስፋፋ የሚችል ስሜት አንጸባርቋል በሚል ነው።

ትላንት እሁዱ በተደረገው የፍርድ ቤት ችሎት የጆኮቪች ጠበቃ ተጫዋቹን ቪዛ ለመቀማት በመንግስት የተሰጡት ማብራሪያዎች ምክንያታዊ አይደሉም ያሉ ሲሆን የቴኒስ ኮከቡን ከአገር ማባረር የፀረ-ክትባት እንቅስቃሴን ያባብሳል ሲሉ አስረድተዋል።

ዕውቁ ጆኮቪች በመጀመሪያ በፈረንጆቹ ታህሳስ ወር አጋማሽ ላይ በኮቪድ መያዙ ተረጋግጦ ነበር። ሆኖም ከዛ በኋላ በአውስትራሊያ የቴኒስ አስተዳደር እና በቪክቶሪያ የግዛት አስተዳደር ወደ አውስትራሊያ መግባት እንዲችል ፍቃድ ተሰጥቶት ነበር።

ሆኖም የአውስትራሊያ የድንበር ዘብ የፌደራል የኮሮናቫይረስ መስፈርቶችን አላሟላም በሚል በፈረንጆቹ ጥር መግቢያ ላይ ቪዛው ተሰርዟል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ሞሪሰን መንግሥት "የአገሪቱን የግዛት አንድነት ለመጠበቅ አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎች እና እርምጃዎችን ለመውሰድ ተዘጋጅቷል" ብሏል።

ሆንም የተቃዋሚው ሌበር ፓርቲ አመራር እና ሴናተር የሆኑት ክሪስቲና ኬኔሊ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጆኮቪች ጉዳይን በተሳሳተ መንገድ በመምራት እራሳቸውን "በዓለም ፊት መሳቂያ" አድርገዋል ሲሉ ተችተዋቸዋል።