ፈረንሳይ ከዩኬ ጋር በስደተኞች ጉዳይ ጥብቅ ውይይት ማድረግ እፈልጋለሁ አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር በስደተኞች ጉዳይ ለንግግር መቀመጥ እንደሚፈልጉ ነገር ግን ይህ ውይይት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት የሚደረግ መሆን እንዳለበት አሳሰቡ።
ዤራርድ ዳርማኒን ይህንን ያሉት 27 ስደተኞች ከፈረንሳይ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለማቋረጥ ሲሞክሩ ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ የአውሮፓ ባለሥልጣናት ባደረጉት ጉባኤ ላይ ነው።
ዩኬ በስብሰባው ብትጋበዝም ከፈንሳይ ጋር በገባችው መቃቃር ምክንያት ሳትሳተፍ ቀርታለች።
የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሯ ፕሪቲ ፓቴል በካሌ በተካሄደው ስብሰባ ሳይገኙ መቅረታቸውን «አሳዛኝ» ሲሉ ገልጸውታል። ነገር ግን በተያዘው ሳምንት ከአውሮፓ ባለሥልጣናት ጋር አስቸኳይ ስብሰባ ለማድረግ ማሰባቸውን ተናግረዋል።
ዩኬ ከስብሰባው የቀረችው ኢማኑኤል ማክሮን የዩናይትድ ኪንግደሙ ቦሪስ ጆንሰን በይፋ ፈረንሳይ እንግሊዝ የገቡ ስደተኞችን መልሳ እንድትወስድ ያቀረቡትን ጥሪ የተመለከተ ምላሽ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው።
ማክሮን ቦሪስን ደብዳቤያቸውን ትዊተር ላይ በማጋራታቸው ነው ቁም ነገረኛነት የጎደለው ሲሉ የከሰሱት።
የዩኬ መንግሥት በበኩሉ ደብዳቤው ከልብ እንደሆነ በመግለጽ ፈረንሳይ የቀረበውን ጥሪ ከግምት እንድታስገባ ጠይቀዋል። ቦሪስም "ይህ በጋራ መፍታት ያለብን ችግር ነው" ብለዋል።
ማክሮን በካሌ እንዲደረግ በጠሩት ስብሰባ ላይ ቤልጄም፣ ፈረንሳይ፣ ኔዘርላንድ፣ ጀርመን እና የአውሮፓ ኮሚሽን ተሳታፊ ሆነውበታል።
በጉባኤው ላይ የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው በዚህ ቀውስ ዙሪያ ከእንግሊዝ ጋር መሥራት እንደምትፈለግ ተናግረዋል።
"ብሪታንያ የአውሮፓ ሕብረትን እንጂ ዓለምን ጥላ አልወጣችም። በብሪታንያ የውስጥ ፖለቲካ ምክንያት ሳንታፈን በእነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያ አጥብቀን መሥራት ይኖርብናል" ሲሉም ተናግረዋል።
አክለውም በርካታ ሰዎች እየሞቱ ነው እናም "ተጨማሪ ሰዎች እንዲሞቱ መፍቀድ የለብንም" ብለዋል።
ዩኬ እራሷን እና ምጣኔ ሀብቷን ለሕገ ወጥ ስደተኞች የማይስብ በማድረግ ኃላፊነት መወጣት አለባት ሲሉ የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ተናግረዋል።












