አሜሪካ እና ኢራን የኒውክሌር ስምምነታቸውን ለማደስ ውይይት ሊጀምሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢራን እና ምዕራባውያን አገራት የኒውክሌር ስምምነት እንዳይቀለበስ ከኢራን ጋር ወሳኝ ውይይት ከአምስት ወራት በኋላ በቪየና ሊጀምር ነው።
አሜሪካን ወደ 2015ቱ ስምምነት መመለስ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ይወያያሉ። ይህም የኢራን የኒውክሌር እንቅስቃሴን የሚገድብ እና በአገሪቱ ላይ ተጣለውን ማዕቀበ ለማንሳት ያግዛለ።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እአአ በ2018 አሜሪካን ከስምምነቱ በማስወጣት ማዕቀቡ ወደ ነበረበት ከመለሱ በኋላ ኢራን ስምምነቱን የሚጥሱ ተግባራትን ፈጽማለች።
ኢራን ስምምነቶቹን ካከበረች ጆ ባይደን ማዕቀቡን ለማንሳት ፈቃደኛ ናቸው። አሜሪካ የመጀመሪያውን እርምጃ እንድትወስድ ኢራን ትፈልጋለች።
የምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ኢራን በዩራኒየም ማበልፀግ መርሃ ግብሯ ቀጥላበት ወደ ኒውክሌር ቦምብ ማምረት ደረጃ በመሻሻሏ ምክንያት ለመደራደር ጊዜው እያለቀ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ኢራን በበኩሏ የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ ለሆኑ አገልግሎቶች እንደሚውል አጥብቃ ትናገራለች።
በኢራን እና በአምስቱ ሀገራት (ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሩሲያ እና ዩናይትድ ኪንግደም) መካከል የተደረገው ውይይት በኦስትሪያ መዲና በተጀመረ ወቅት የአሜሪካ ተወካዮች ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ተሳታፊ ሆነዋል።
አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ለኒውዮርክ ታይምስ እንደተናገሩት በዋሽንግተን እና በቴህራን ምን እርምጃ መወሰድ እንዳለበት እና መቼ በሚለው ላይ "አጠቃላይ ስምምነት የተጠናቀቀው" በሰኔ ወር ከተካሄደው የኢራን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፊት ነው።
ከባራክ ኦባማ አስተዳደር ጋር ለስምምነቱ ሲደራደሩ የነበሩትን ሃሰን ሩሃኒን ለመተካት በተካሄደው ፉክክር የምዕራባዊያን ተቺ የሆኑት ኢብራሂም ራይሲ አሸንፈዋል።
ራይሲ በነሐሴ ወር ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ውይይቱ እንዲራዘም እንደማይፈቅዱ ቃል ገብተዋል። ሆኖም እስከዚህ ወር መጀመሪያ ድረስ ወደ ቪየና ለመመለስ አልተስማሙም።
የኢራን ተደራዳሪዎች የኢራንን ጥቅሟን ለማስጠበቅ በምንም መልኩ ወደ ኋላ እንደማይሉም ገልጸዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካ "ጥፋተኛነቷን እንድታመን" እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። በተጨማሪም በአሜሪካ የተጣሉ ሁሉም ማዕቀቦች በፍጥነት እንዲነሱ እና ቀጣይ የሚመጡ የአሜሪካ ፕሬዝደንቶችም ስምምነቱን ጥለው እንደማይወጡ "ዋስትና" እንደሚፈልጉም ገልጸዋል።
የባይደን የኢራን ልዩ መልዕክተኛ ሮበርት ማሌይ በበኩላቸው አገራቸው የኢራንን ኢኮኖሚ ያሽመደመደውን የትራምፕ አስተዳደር የጣለውን ማዕቀብን ማንሳት ጨምሮ ወደ ስምምነቱ ለመመለስ አስፈላጊ የሆኑትን ሁሉንም እርምጃዎች ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል ።
ማሌይ አክለውም ከኢራን ጋር የሚደረገው "የድርድር መስኮት…ሁሌም ክፍት ላይሆን ይችላል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ኢራን ሊከማች በሚችለው የቁሳቁስ ገደብን ለመወሰን ተስማምታለች። እነዚህም የሚበለጽግበት ደረጃ፣ ማበልጸግ ለማካሄድ ጥቅም ላይ የሚውሉ ማሽኖች ቁጥር እና ዓይነት እንዲሁም ሊካሄድ የሚችልባቸው ቦታዎችን ያጠቃልላል።
ይሁን እንጂ ኢራን ከተፈቀደው በላይ ብዙ እጥፍ የሚበልጥ የበለፀገ ዩራኒየም አከማችታለች።
የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ተቆጣጣሪዎች የኢራንን የኒውክሌር ስፍራዎችን እንዳይጎበኙ ተገድበዋል።












