ከአገር የወጡት የሰሜን ኮሪያ ኮሎኔል ይፋ ያደረጉት የመንግሥት ምስጢር

ከ30 ዓመታት በላይ በሰሜን ኮሪያ መንግሥት ውስጥ ሲያገለግሉ የነበሩት ኮሎኔል ኪም ኩክ-ሶንግ የሰሜን ኮሪያ መንግሥትን ምስጢር ይፋ አደረጉ።

የሰሜን ኮሪያ መንግሥትን ለሦስት አስርት ዓመታት ያገለገሉት ኮሎኔል ኪም ኩክ-ሶንግ፤ ከአገር ከድተው ሲወጡ የአገሪቱ የስለላ ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊ ነበሩ።

ኮሎኔሉ ይሰሩበት የነበረው የሰላለ ኤጀንሲ፤ የሰሜን ኮሪያ መንግሥት መሪዎች "አይን፣ ጆሮ እና አእምሮ ነው" ይላሉ።

ኮሎኔሉ የአገሪቱ መሪዎችን ምስጢር ስለመያዛቸው፣ ጸረ-መንግሥት አቋም የሚያራምዱ ተቺዎችን ለመግደል ገዳዮችን ስለመላካቸው እና ለመንግሥት ፕሮፖጋንዳ ገንዘብ ለማሰባሰብ ሕገ-ወጥ ዕጽ ማምረቻ ላብራቶሪ ማቋቋማቸውን ይናገራሉ።

እኚህ ከፍተኛ የቀድሞ የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ባለስልጣን ከፒዮንግያንግ የሸሹት እአአ 2014 ላይ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ለደቡብ ኮሪያው የስለላ ተቋም ይሰራሉ።

አደንዛዥ ዕጽ፣ ጦር መሳሪያ እና ሽብር

ኮሎኔል ኪም ኩክ-ሶንግ የሰሜን ኮሪያ መንግሥት በየትኛውም አማራጭ ገንዝብ ለማግኘት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም ይለም ይላሉ።

የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ገንዘብ ለማግኘት በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ አገራት ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና አደንዛዥ ዕጽ ዝውውር እንደሚያካሂድ ይናገራሉ።

ኮሎኔል ኪም ኩክ-ሶንግ እአአ 2009 ላይ "የሽብር ግብረ ኃይል" እንዲቋቋም የሚያዝ ትዕዛዝ ከከፍተኛ የሰሜን ኮሪያ አመራር ደረሰን ይላሉ።

የዚህ ግብረ ኃይል ተልዕኮ ደግሞ ከሰሜን ኮሪያ ከድተው ወደ ደቡብ ኮሪያ የሸሹ ባለስልጣናትን አድኖ መግደል መሆኑን ኮሎኔሉ ያስረዳሉ።

"ህዋንግ ጃንግ-ዮፕ ለመግደል የተቋቋመውን ቡድኑ እኔ በግሌ መርቻለሁ" ይላሉ።

ህዋንግ ጃንግ-ዮፕ አገር ከድተው ወደ ደቡብ ኮሪያ ከመሸሻቸው በፊት ከሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል አንዱ ነበሩ። እኚህ ግለሰብ እአአ 1997 ላይ ከፒዮንግያንግ ከሸሹ በኋላ የሰሜን ኮሪያ አመራርን አጥብቀው ይቃወሙ ነበር።

ይህም የወቅቱ የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኢልን በጣም ያበሳጭ ነበር በማለት ኮሎኔል ኪም ኩክ-ሶንግ ያስታውሳሉ። ለዚህም የኪም ጆንግ-ኢል ቤተሰብ ሰውዬውን መበቀል ፈለገ።

ኮሎኔሉ ህዋንግ ጃንግ-ዮፕን የመግደል ውጥን ግን እንደታሰበው አልሄደም ይላሉ። በአሁኑ ወቅት በዚህ የግድያ ሙከራ ተሳትፈዋል የተባሉ ሁለት የሰሜን ኮሪያ የጦር መኮንኖች በደቡብ ኮሪያ አስር ቤት ይገኛሉ።

"ሰላይ በሰማያዊው ቤት ውስጥ"

"ሰማያዊው ቤት" በሰሜን ኮሪያ የደኅንነት አባላት ለደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንታዊ ጽህፈት ቤት የተሰጠ መለያ ስም ነው።

ኮሎኔሉ በሰሜን ኮሪያ የሰለላ ተቋም ውስጥ ካላቸው የሥራ ኃላፊነቶች መካከል፤ የደቡብ ኮሪያን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በቅርብ ርቀት መከታተል ነው።

ይህም ዓይን እና ጆሮ የሆኑ ሰላዮችን በደቡብ ኮሪያ ማሰማራትን ይጠይቃል ይላሉ።

"ሰላዮች ወደ ደቡብ ኩሪያ እንዲሄዱ ያዘዝኩባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው" ይላሉ ዝርዝር መረጃ ከመሰጠት በመቆጠብ።

"የሰሜን ኮሪያ ሰላይ በደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንታዊ ቢሮ ተልዕኮውን ፈጽሞ በሰላም ወደ ሰሜን ኮሪያ የተመለሰበት አጋጣሚ አለ። ይህ 1990ዎቹ (እአአ) መጀመሪያ ላይ ነበር። ለአምስት ወይም ለስድስት ዓመታት ለሰማያዊው ቤት ከሠራ በኋላ ተምልሶ ለሰሜን ኮሪያ መስራት ጀምሯል" ይላሉ።

"ላረጋግጥላችሁ የምችለው የሰሜን ኮሪያ ሰላዮች በተለያዩ የደቡብ ኮሪያ ድርጅቶች ውስጥ ሥራዎችን ያከናውናሉ ይገኛሉ" ይላሉ ኮሎኔል ኪም ኩክ-ሶንግ።

ቢቢሲ የኮሎኔል ኪም ኩክ-ሶንግ ቃል ትክክለኛነትን ማረጋገጥ የሚችልበት መንገድ የለም።

ሰሜን ኮሪያ ከዓለማችን ድሃ አገራት አንዷ ልትሆን ትችላለች። ከተቀረው ዓለምም ተነጥላ ትገኛለች። ይሁን እንጂ ምስጢራዊ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ውስብስብ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ትጠቀማለች። ከ6ሺህ በላይ የሰለጠኑ መረጃ መንታፊዎች ስለማሰልጠኗም የነገራል።

እንደ ኮሎኔል ኪም ከሆነ የቀድሞ ፕሬዝደንት ኪም ጆንግ-ኢል አገራቸው ለሳይበር ጦርነት ዝግጁ እንድትሆነ ካዘዙ በኋላ፤ ከመላው ሰሜን ኮሪያ ብሩህ አእምሮ ያላቸውን ተማሪዎች በመሰብሰብ ለስድስት ዓመታት የሚዘልቅ ልዩ ትምህርት እንዲወስዱ ተደርጓል።

ሰሜን ኮሪያ ሄሮይን እና ኦፒየም የተሰኙ አደንዛዥ ዕጾችን አምርታ እንደምትሸጥ ከዚህ በፊት ተጠቁሟል። የአገሪቱ መንግሥት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማግኘት ሲል አደንዛዥ ዕጾችን ያዟዙራል።

ከዚህ በተጨማሪ የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ጦር መሳሪያዎችን እንደ ኢራን ላሉ መንግሥታት በመሸጥ የገቢ ምንጩን ያሳድጋል።

ኮሎኔሉ እንደሚሉት ከሆነ ፒዮንግያንግ ለረዥም ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት ለመታመሱ አገራት ጦር መሳሪያዎችን እና የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂዎችን ትሸጣለች።

በተመሳሳይ የተባባሩት መንግሥታት ሰሜን ኮሪያ ለሶሪያ፣ ምያንማር፣ ሊቢያ እና ሱዳን ጦር መሳሪያ ታቀርባለች ሲል ክስ አቅርቦ ነበር።

ከአገር የመሸሽ ውሳኔ

ኮሎኔል ኪም የትውልድ፤ የአያቶቼ አገር ከሚሏት አገራቸው ሰሜን ኮሪያ ወደ ደቡብ ኮሪያ የመሸሽ ውሳኔ ቀላል እንዳልነበረ ይናገራሉ።

ለዚህ ውሳኔ የዳረጋቸው ደግሞ የረዥም ጊዜ የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ-ኡን ሞት በኋላ የተተኩት ወጣቱ ኪም ጆንግ-ኡን ያልታሰበ እርምጃ መሆኑን ይናገራሉ።

እአአ 2011 ላይ ኪም ጆንግ-ኡን ወደ ስልጣን ሲመጡ ስልጣናቸውን ሊገዳደር የሚችልን በሙሉ ማስወገድን ተያያዙ። ኪም ጆንግ-ኡን የገዛ አጎታቸውን ሳይቀር ማስገደላቸው ያልተጠበቀ እና አስደናጋጭ ነበረ ይላሉ ኮሎኔል ኪም።

የረዥም ጊዜ የሰሜን ኮሪያ መሪ ጤና ሲርቃቸው ቀጣዩ መሪ ጃንግ ሶን-ታኤክ ይሆናሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ነገር ግን ኪም ጆንግ-ኡን መንበረ ስልጣኑን ከያዙ በኋላ፤ የአጎታቸውን መገደል በመገናኛ ብዙኃን አስነገሩ።

"እጅግ በጣም ነው የተገረምኩት። ከፍተኛ ድንጋጤ" ይላሉ ኮሎኔል ኪም። "ወዲያውኑ ለሕይወቴ ሰጋሁ። በሰሜን ኮሪያ ልኖር እንደማልችል ግልጽ ሆነልኝ" ይላሉ።

ከዚያ ቅጽበት ጀምሮ ከቤተሰቤ ጋር ከሰሜን ኮሪያ መውጣት ስለምችልበት ሁኔታ ማሰብ ጀምርኩ ይላሉ።