ዚምባብዌ ያልተከተቡ የመንግሥት ሠራተኞችን ከሥራ አገደች

ዚምባብዌ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ያልተከቡ የመንግሥት ሠራተኞቿን ወደ ሥራ ቦታ አትምጡ፣ ታግዳችኋል ብላለች።

የማስታወቂያ ሚኒስትሯ ሞኒካ ሙትስዋንግዋ መንግሥት ሠራተኞቹ የኮቪድ -19 ክትባቶችን እንዲከተቡ "በቂ ጊዜ" ሰጥቷል ብለዋል።

ባለሥልጣናቱ እንደሚሉት በኮሮናቫይረስ ታመው ሆስፒታል ከገቡት ሰዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ያልተከተቡ ናቸው።

አገሪቱ በአማካኝ በየቀኑ 145 አዳዲስ ታማሚዎችን እያገኘች ሲሆን ማክሰኞ ሰባት ሰዎች በወረርሽኙ ሰበብ መሞታቸውን ሪፖርት አድርጋለች።

በአገሪቱ ውስጥ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ዚምባብዌውያን ማለትም 12 በመቶ ገደማ የሚሆነው ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ተከትቧል ተብሏል።

በካቢኔው ውሳኔ ምን ያህል የመንግሥት ሠራተኞች እንደሚጎዱ ወይም ደመወዛቸውን መቀበላቸውን ይቀጥሉ ወይም ከቤት ሆነው መሥራት ይችሉ እንደሆነ የተገለጸ ሁኔታ የለም።

በዚምባብዌ ውስጥ መንግሥት የአገሪቱ ትልቁ ቀጣሪ ሲሆን ይህ የእግድ መመሪያም እንደ የጤና እንክብካቤ አሰጣጥ እና ትምህርት ባሉ አገልግሎቶች ላይም ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።

አብዛኛዎቹ የመንግሥት ትምህርት ቤት መምህራንም እስካሁን አልተከተቡም።

በዚህ ወር በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነሱን ተከትሎ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ ምግብ ቤቶች እና አብያተ ክርስቲያናት እንደገና እንዲከፈቱ ተፈቅዷል። ነገር ግን ሠራተኞቹ እና ደንበኞች ሙሉ በሙሉ መከተብ አለባቸው።

የሠራተኛ ማኅበራት በበኩላቸው ባልተከተቡ ሠራተኞች ላይ አድልዎ ተፈፅሟል በሚል በርካታ ኩባንያዎችን ወደ ፍርድ ቤት ወስደዋል።