በትግራይ የነዳጅ እና የገንዘብ እጥረት መከሰቱ ተገለጸ

መቀለ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

የምስሉ መግለጫ, መቀለ ከተማ ሕዳር ወር ላይ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) በትግራይ ክልል የነዳጅ እና የጥሬ ገንዘብ እጥረት መከሰቱን የሚያመላክቱ ሪፖርቶች ደርሰውኛል አለ።

ኦቻ የነዳጅ እና የገንዘብ እጥረቱ የሰብአዊ እርዳታ ሥራውን የበለጠ አስቸጋሪ ሊያደርገው እንደሚችል ገልጿል።

ባለፈው ሰኞ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል ለቆ እንደወጣና አካባቢዎቹ በአማጺያን እጅ መግባታቸው ይታወሳል።

ኦቻ ባወጣው የሁኔታ ሪፖርት ላይ እንዳሰፈረው በትግራይ ያለው ተለዋዋጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ቢገባም ከአጋሮቹ በክልሉ አንፃራዊ ሰላም እንዳለ መረዳቱን አመልክቷል።

በክልሉ የቴሌኮምዩኒኬሽን፣ የኤሌክትሪክ ብሎም መሰል መሰረታዊ አቀርቦቶች ተቋርጠው ይገኛሉ ሲልም አክሏል።

ወደ ትግራይ ክልል የሚወስዱ አራቱም መግቢያ እና መውጫ በሮች ዝግ መሆናቸውን ብሎም በትግራይ ውስጥም የትራንስፖር እቅስቃሴ እንደቆመ ኦቻ ተረድቻለሁ ብሏል።

የእርዳታ ሠራተኞችም በሳተላይት ስልክ ላይ ተመስርተው እንደሚገኙ አክሏል። ይህም አገልግሎት በመቀለ ውስጥ ባሉ ሠራተኞች ብቻ የተገደበ ነው።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፌደራል መንግሥቱ በክልሉ ሰብአዊነትን መሠረት ያደረገ የተኩስ አቁም እንዲደረግ መጠየቁን ተከትሎ የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁ ይታወሳል።

ላለፉት ሁለት ሳምንታት በመቀለ እና አዲግራት (ምሥራቃዊ ትግራይ)፣ አቢ አዲ (ማዕከላዊ) እና ደቡብ የትግራይ አካባቢዎች ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ በታጠቁ አካላት ክልከላዎች እንደነበሩ ኦቻ ገልጿል።

ከሳምንት በፊት በማዕከላዊ ዞን ሦስት የኤምኤስኤፍ ባልደረቦች መገደላቸውን ተከትሎ የሰብአዊ ተቋማት ሠራተኞቻቸውን በማስወጣት ጅራቸውን አቁመዋል፤ ይህም የሕዝቡ የጤና አጠባበቅ እና የነፍስ አድን ድጋፍ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯልም ተብሏል።

አጋር ድርጅቶቹ ሠራተኞቻቸውን ከአክሱም እንዲሁም ከሳምረ እንዲወጡ አድርገዋል፣ የታጠቁ አካላት የእርዳታ ድርጅቶቹ ባልደረቦች ወደ ሳምረ እንዳይሄዱ እንቅፋት ነበሩ፣ የህክምና እና የምግብ አቅርቦቶችም ከእርዳታ አጓጓዦች ላይ ተነጥቀዋል ሲል ኦቻ ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎችን ጨምሮ አጋር ድርጅቶች የመከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ የተለያዩ ታጣቂዎች በመቀሌ፣ በዳንሻ እና በአብዱራፊ የሚገኙ የቴሌኮምዩኒኬሽን መሣሪያዎችን መውሰዳቸውንም ኦቻ ገልጿል።

ባለፉት ቀናት ውስጥ ጉልህ የሆነ የደኅንነት ክስተቶች አለማጋጠማቸውን እና የእርዳታ አጋሮችም ሥራቸውን በተለያዩ አማራጭ እያካሄዱ ነውም ተብሏል።

የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ሠራተኞች ከመኖሪያ ቤታቸው ወይም ከሆቴል ሆነው ሥራቸውን እያከናወኑ ሲሆን የመስክ ተልዕኮዎች ለግዜው መታገዳቸውንም ተቋሙ አስታውቋል።

የኤርትራ እና የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይሎች ከአብዛኛው የትግራይ ክልል መውጣታቸውን እና የአማራ ክልል ኃይሎች ግን በደቡብ ፣ በምዕራብ እና በሰሜን ምዕራብ ትግራይ የሚገኙትን አካባቢዎች ለቀው እንደማይወጡ መግለጻቸውን አስታውሷል።

የአማራ ልዩ ኃይልም በተከዜ ወንዝ ምዕራብ እና ደቡብ የሚገኙ ቦታዎችን አለመልቀቁን እና ሐምሌ 25/2013 ቀን ጎንደርን ከትግራይ የሚያገኛኘው በተከዜ ወንዝ ላይ ያለው ድልድይ በአማራ ልዩ ኃይል በተደረገ ፍንዳታ መፍረሱን ኦቻ ጨምሮ ገልጿል።