የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ ጉዳይ ላይ ዛሬ ይመክራል

የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት። (ከሌላ ስብሰባ ላይ የተወሰደ ፎቶ)

የፎቶው ባለመብት, © EVAN SCHNEIDER

የምስሉ መግለጫ, የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት። (ከሌላ ስብሰባ ላይ የተወሰደ ፎቶ)

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ የትግራይ ሁኔታ ላይ ለመምከር ስብሰባ ጠርቷል፡፡

ይህ ስብሰባ በ8 ወራት ውስጥ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በግልጽ የሚመክር የመጀመርያው ሸንጎ ይሆናል፡፡

የቢቢሲ ኒውስዴይ የራዲዮ መርሐግብር በጉዳዩ ላይ በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑትን ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድን አጭር ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸው ነበር፡፡

አምባሳደር ሊንዳ በኢትዮጵያ ጉዳይ መነጋገራችን እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው ካሉ በኋላ፣ "በዚህ ጦርነት ውስጥ እጃቸው ያለበት አካላት ማወቅ ያለባቸው የጸጥታው ምክር ቤት አሁኑኑ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ማየት እንደሚሻ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል በረሀብ አፋፍ ላይ ናቸው ያሉት አምባሳደሯ፣ ይህ ደግሞ ረሀብን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀም ነው ሲሉ ከሰዋል፡፡

"ሁላችንም የጸጥታው ምክር ቤት አባላት፣ 15ታችንም ማለት ነው፣ ይህ ጉዳይ አንገብጋቢ እንደሆነ በጽኑ እናምናለን፡፡ ልዩነት ያለን እንዴት ጉዳዩ ይፈታ በሚለው አካሄድ ላይ ነው፡፡" ያሉት አምባሳደር ሊንዳ ግሪንፊልድ ዞሮ ዞሮ "የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ አንዳች ውሳኔ ላይ መድረስ እንዳለበት በሁላችንም የሚታመን ነው፤ አያጠራጥርም" ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበሩ ሸንጎዎች ላይ ምን ተወስኖ ነበር?

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ከዚህ ቀደም ለመጀመሪያ ጊዜ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል በቂ የሰብዓዊ እርዳታ ባይቀርብም የኢትዮጵያ መንግሥት ጥረት ግን የሚበረታታ እንደሆነ ገልጾ ነበር፡፡

የምክር ቤቱ አባል አገራት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የፖለቲካ ነጻነትን ያከብራሉ ብሎ ነበር በዚህ ስብሰባ።

የመግለጫውን መውጣት ተከትሎ የተመድ የኢትዮጵያ ተወካይ፤ የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ለሰጡት 'ገንቢ ምልከታ እና ድጋፍ' አድናቆቱን ገልጿል።

በአንጻሩ ጾታዊ ጥቃቶችን ጨምሮ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ያሳስቡኛል ያለው ምክር ቤቱ፤ ጥሰቶቹ በገለልተኛ አካል እንዲመረመሩ እና ተጠያቂዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ መጠየቁ አይዘነጋም፡፡

በዚህ ረገድም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በጋራ የሚያደርጉትን ምርመራ በበጎ ጎኑ ተቀብሎት ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤቱ ኢትዮጵያን በተመለከተ መግለጫ ለማውጣት በርካታ ጊዜ ቢሰበሰብም ከስምምነት ሳይደርስ መቅረቱ ይታወሳል።

የካቲት 25/2013 ዓ.ም የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን በተመለከተ ያደረገው ውይይት ከስምምነት ላይ ሳይደርስ መቅረቱን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።

የዜና ወኪሉ የጸጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ባረጋገጠ መልኩ በትግራይ አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ እና ግጭት እንዲቆም የሚጠይቅ መግለጫ ለማውጣት ያደረገው ስብሰባ በሩሲያ እና በቻይና ተቃውሞ ሳይወጣ ቀርቶ ነበር።

ሩሲያ እና ቻይና መግለጫው በኢትዮጵያ "ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው" በማለት ነበር ተቃውሟቸውን ያሰሙት።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ አሜሪካ በሉዓላዊ አገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንድትቆጠብ ጠይቆ ነበር።

ሩሲያና ቻይና በተቃወሙት ስብሰባ ላይ ሌሎች አባላት ምን ብለው ነበር?

የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ግድያዎችን በተመለከተ የሚወጡት ሪፖርቶች አሳሳቢ እንደሆኑ ገልጾ፤ የሰብአዊ ሁኔታውን በተመለከተ ያለው መረጃ መሬት ላይ ያለው እውነታ ነጸብራቅ እንደሆነ ገልጿል።

በተጨማሪም አስፈላጊውን እርዳታ ለማቅረብ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፉ ከፍ እንዲል ተጨማሪ ሐብት እንደሚያስፈልግም አመልክቷል።

የጸጥታው ምክር ቤት አባል አገራት የትኞቹ ናቸው?

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት 15 አባል አገራት አሉ።

ከ15ቱ አባል አገራት አምስቱ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ቋሚ አባል አገራት ሲሆኑ፤ አስሩ ደግሞ በየዓመቱ የሚቀያየሩ እና ድምጽን በድምጽ የመሻር አቅም የሌላቸው አባል አገራት ናቸው።

ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው የምክር ቤቱ አባላት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ቻይና ናቸው።

ኢስቶኒያ፣ ሕንድ፣ አየርላንድ፣ ኬንያ፣ ሜክሲኮ፣ ኒጂር፣ ኖርዌይ፣ ሴንት ቪንሰንት ኤንድ ዘ ግሬናዲንስ፣ ቱኒዚያ እና ቬትናም ደግሞ አስሩ ተለዋዋጭ የምክር ቤቱ አባላት ናቸው።