የተከዜን ድልድይ ማን አፈረሰው?

የተከዜ ድልድይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፌደራሉ መንግሥት በተከዜ ወንዝ ላይ የነበረውን ድልድይ ያፈረሰው የህወሓት ኃይሎች ናቸው ሲል የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ ድልድዩን የአማራ ልዩ ኃይል ማፈረሱን የሚያመላክት ሪፖርት ደርሶኛል ብሏል።

በትግራይ ክልል የሚገኘው እና ጎንደርን ከሽሬ የሚያገናኘው ግዙፉ የተከዜ ድልድይ መፍረሱን የተለያዩ የእርዳታ ሰጪ ተቋማት ትናንት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የተከዜ ድልድይ አደጋ እንደደረሰበት ካስታወቁ ድርጅቶች መካከል የዩናይትድ ኪንግደም ዓለም አቀፍ እርዳታ ድርጅት ሬስኪዩ ዩኬና የተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ቢሮ [ኦቻ] ይገኙበታል።

ምንም እንኳ እነዚህ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ድልድዩን ማን እንዳፈረሰው ያሉት ነገር ባይኖርም የድልድዩ መፍረስ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱን እንደሚጎዳ ገልጸዋል።

"ድልድዩን ያፈረሰው ህሓት ነው"

የኢትዮጵያ መንግሥት ለድልድዩ መፍረስ ህወሓትን ተጠያቂ አድርጓል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር የተቋቋመው የመረጃ ማጣሪያ ክፍል "ህወሓት ሆን ብሎ ነው የተከዜ ድልድይን ያፈረሰው" ሲል በማኅበራዊ ድር አምባ ገፁ አስፍሯል።

መንግሥት፤ ህወሓት "ሆን ብሎ ድልድዩን ያፈረሰው በሥፍራው ያለውን የእርዳታ ሥራ ለማወክ ነው" ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ቢሮ (ኦቻ) በበኩሉ ጎንደርና ሽሬን የሚያገኛው የተከዜ ድልድይ ሰኔ 25/2013 በአማራ ልዩ ኃይል ከጥቅም ውጪ እንዲሆን እንደተደረገ የሚጠቁም መረጃ አለ ብሏል።

ኦቻ ትግራይን በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት ላይ በትግራይ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢንተርኔትና ቴሌኮሚዩኒኬሽን አቅርቦት መቋረጥ ከድልድዩ መውደም ጋር ተዳምሮ የእርዳታ አቅርቦት ሥራውን ይበልጥ እንደሚያስተጓጉል አመልክቷል።

ኦቻ በድረ ገፁ ባወጣው ወቅታዊ ሪፖርት የአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች ከምዕራባዊ ትግራይ አካባቢዎች ለቀው አልወጡም ይላል።

የእርዳታ አስተባባሪው ድርጅት በተጨማሪ በትግራይ ክልል የጥሬ ገንዘብና የነዳጅ እጥረት እያጋጠመ ነው ሲል አስነብቧል።

ላለፉት ሁለት ሳምንታት በመቀለና አዲግራት ከተሞች የነበረው የእርዳታ ሥራ በታጠቁ ኃይሎች ምክንያት መደናቀፉን ድርጅቱ ቢያስታውቅም የትኛው ወገን መንገድ እንደዘጋ አልጠቆመም።

line

በትግራይ ክልል በፌደራል መንግሥቱና በህወሓት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት አሁንም እልባት አላገኘም።

የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮች በርካታ የትግራይ ክልል ሥፍራዎችን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ ከሰሞኑ የትግራይ መከላከያ ኃይል የክልሉን መዲና ጨምሮ ሌሎች ስፍራዎችን መልሶ መያዙ ይታወሳል።

የሕወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት ጌታቸው ረዳ የመንግሥት ኃይል ከመቀለና ሌሎች ከተሞች ተሸንፎ ነው የወጣው ቢሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግን ይህ ሀሰት ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ሰኔ 22/2013 ዓ.ም በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለጋዜጠኞች ባደረጉት ገለጻ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ባደረጉት ንግግር "ጦሩ የወጣው በሽንፈት ሳይሆን ኦፕሬሽኑ (ዘመቻው) በመሳካቱ ነው" ብለዋል።

line

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሳምንታት በፊት ባደረገው ግምገማ የክረምቱ ዝናብ ከመጀመሩ በፊት በአስቸኳይ ወደ ተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ድጋፍ እንዲደርስ ካልተደረገ በ1977 ዓ.ም በአገሪቱ የተከሰተው አይነት በርካቶችን ለሞት የሚዳርግ ከባድ የሰብአዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ አሜሪካ፣ የአውሮፓ አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መንግሥት "ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እያዋለ ነው" በሚል በመክሰስ ያልተገደበ የእርዳታ አቅርቦት እንዲመቻች፣ የተኩስ አቁም እንዲደረግና በበርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚከሰሱት የኤርትራ ወታደሮች እንዲወጡ ሲወተውቱ ቆይተዋል።

በክልሉ አምስት ሚሊዮን ያህል ነዋሪዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሆነ 350 ሺህ ሕዝብ የሚሆነው በረሃብ ቋፍ ላይ ነው።