ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምርጫ 2013፡የጳጉሜ 1 ምርጫ በየትኞቹ አካባቢዎች ይካሄዳል?
መጪው ስድስተኛ አገራዊ ምርጫ ሰኔ 14/ 2013 ዓ.ም ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት ሲሆን በዚህ ቀን ምርጫ ማካሄድ ባልተቻለባቸው አካባቢዎች በተለዋጩ ቀን ጳጉሜ 1/ 2013ዓ.ም እንዲካሄድ መወሰኑን ከምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው ሰኔ 3፣ 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ነው።
በፀጥታ ችግር ምክንያት ጳጉሜ 1 ምርጫ ከሚደረግባቸው ስፍራዎች መካከል በቤንሻንል ጉሙዝ ክልል (መተከል ሺናሻ ልዩ፣ ካማሻ እና ዳለቲ)፣ በኦሮሚያ ክልል (ቤጊ፣ ሰኞ ገበያ፣ አያና፣ገሊላ፣አሊቦ፣ጊዳሚ፣ ኮምቦልቻ)) ይገኙበታል።
በተጨማሪም በአማራ ክልል (ማጀቴ (ማኮይ)፣ አርጎባ ልዩ፣ ሸዋሮቢት፣ ኤፌሶን፣ ጭልጋ 1፣ ጭልጋ 2፣ ላይ አርማጭ፣ አንኮበር)፣ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ( ሱርማ ልዩ ፣ ዲዚ ልዩ፣ ቀይ አፈር መደበኛ፣ ማጀት መደበኛ፣ ሸኮ ልዩ፣ ቴፒ) ና በሐረሪ ክልል (ጀጎል ልዩ ፣ ጀጎል መደበኛ ) ጳጉሜ 1 ምርጫ ከሚደረግባቸው ስፍራዎች መካከል ተካትተዋል።
በዚሁ ቀንም በሚደረገው ምርጫ የፀጥታው ሁኔታ እንዲሻሻል ኃላፊነት ያለባቸው የመንግሥት የፀጥታ አካላት ዝግጅት እንዲያደርጉም ምርጫ ቦርድ ጥሪውን አቅርቧል።
ከዚህም በተጨማሪ ለ54 የምርጫ ክልሎች በታተሙ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ላይ የተለያዩ ጉድለቶች መገኘቱን ያስታወቀው ምርጫ ቦርድ አማራጭ መፍትሄዎችንም ለመፈለግ ከፓርቲዎች ጋር ምክክር አድርጓል።
ቦርዱ እንዳስታወቀው በፍጥነት ህትመት ሊከናወንባቸው የሚችልባቸውን መንገዶች እየፈለገ ሲሆን የድምፅ መስጫ ወረቀት ጉድለት ካለባቸው መካከል በ27ቱ የምርጫ ክልሎች ጳጉሜ 1 ምርጫ እንዲካሄድ ተወስኗል።
በሶማሌ ክልል በ14 የምርጫ ክልሎች ላይ ድምፅ የመስጠት ሂደት ላይ ችግር አለ የሚል ሪፖርት ደርሶት እሱን በምርመራ ማጠናቀቁን አስታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ የድምፅ መስጫ ወረቀት ጉድለት ከተገኘባቸውና ድጋሚ እንዲታተሙ ከተወሰኑት መካከል 14ቱ በሶማሌ ክልል ይገኛሉ።
ከነዚህም ጋር ተያይዞ በሶማሌ ክልል የሚደረገው ምርጫ ጳጉሜ 1፣ 2013 ዓ.ም እንዲሆን መወሰኑን በመግለጫው አስታውቋል።
ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተጨማሪ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ከምርጫው ጋር ሰኔ 14 በአንድ ቀን እንዲካሄድ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ጳጉሜ 1/2013 ዓ.ም እንዲካሄድ ተወስኗል።
ቦርዱ እንዳሳወቀው "ህዝበ ውሳኔው በሚከናወንባቸው ምርጫ ክልሎች በጸጥታ ችግር የተነሳ ድምጽ የማይሰጥባቸው ምርጫ ክልሎች በመኖራቸው የህዝበ ውሳኔውን ምእሉነት ስለሚያጎድለው እና የሁሉንም መራጮች ምርጫ በትክክል መመዘን ስለማይቻል ነው" ብሏል።
ሊካሄድ አስር ቀናት በቀሩት 6ኛው ብሔራዊ ምርጫ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 37.4 ሚሊዮን መሆኑንም ምርጫ ቦርድ በዛሬው ዕለት በማህበራዊ ትስሰር ገፁ ባወጣው መረጃ አስፍሯል።
ቦርዱ እንዳለው አኃዙ በሶማሌ ክልል በምርመራ የተነሳ የመራጮች ምዝገባ የታገደባቸው 14 የምርጫ ክልሎችን እንደማይጨምርም ተጠቅሷል።
ከዚህም በተጨማሪ ከቦርዱ እውቅና ውጭ የተከፈቱ በአዲስ አበባ 2፣ በድሬዳዋ፣ 6፣ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል 71 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተደረጉ የመራጮች ምዝገባዎች ህጋዊ አይደሉም በማለት ቦርዱ መወሰኑ ሰፍሯል።