ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ በተከሰሰው በቀድሞ የፖሊስ አባል ጉዳይ ዛሬ ውሳኔ ይሰጣል
በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ የተከሰሰው የቀድሞ የሚኒያፖሊስ ፖሊስ አባል ዴሪክ ሾቪን ጉዳይ ዛሬ ብይን ይሰጣል።
ይህንንም ተከትሎ ጉዳዩ እየታየ የሚገኝበት ፍርድ ቤት ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገለት ይገኛል።
የሚሰጠው ብይን ምንም ይሁን ምን በመላው አገሪቷ በሚገኙ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ሊቀሰቀሱ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።
ከሳሾች እና በጠበቆች ለሶስት ሳምንታት የዘለቀ ክርክር ካደረጉ በኋላ ነው ዛሬ ብይን የሚሰጠው።
ከሳሾች የቀድሞው ፖሊስ አባል ጆርጅ ፍሎይድን ገድሏል ብለው ጉዳዩን እየመረመሩ ለሚገኙት ዳኞች የተናገሩ ሲሆን፤ የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ዴሪክ ሾቪን የፖሊስ ልምምድን እየተከተለ ነበር ብለዋል።
የተከሳሽ ጠበቆች ምን አሉ?
የቀድሞ ፖሊስ አባል ጠበቃ ኤሪክ ኔልሰን፤ ደንበኛቸው አካሉ ግዙፍ የሆነ እና ከሶስት የፖሊስ አባላት ጋር ሲታገል የነበረን ተጠርጣሪ በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ የወሰደውን እርምጃ የትኛውም የፖሊስ አባል ሊያደርገው የሚችለው ነው ሲሉ ተከራክረዋል።
ጠበቃው ጨምረውም ጆርጅ ፍሎይድ ከፍተኛ መጠን ያለው እጽ ወስዶ ነበር ብለዋል።
ደንበኛቸውም የሚወስደው ተግባር በሙሉ በተንቀሳቃሽ ምስል እንደሚቀረጽ ስለሚያውቅ ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ሆነ ብሎ አይወስድም ብለዋል።
ከሳሾችስ ምን አሉ?
ዐቃቤ ሕጉ ስቲቭ ስቼሌቸር፤ ጉዳዩን እየመረመሩ ለሚገኙት ዳኞች፤ ዴሪክ ሾቪን በጆርጅ ፍሎይድ ላይ ከ9 ደቂቃዎች በላይ በጉልበቱ ተጭኖ የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምስል በማጣቀስ "የምታዩትን እመኑ። ያያችሁትን አይታችኋል" በማለት ተናግረወል።
የቀድሞ የፖሊስ አባል ተግባር የፖሊስ ሳይሆን ግድያ ነው ብለውም ተናግረዋል ከሳሹ።
በቀጣይ ምን ይሆናል?
የጆርጅ ፍሎይድን ጉዳይ ለመመርመር የተሰየሙት ዳኞች 12 ናቸው። 7 ሴቶች እና 5 ወንዶች። ከእነዚህ መካከል 4ቱ ጥቁር አሜሪካውያን ናቸው።
ይህ የዳኞች ቡድን በቀጣይ የ45 ሰዎች ምስክርነትን ሊሰማ ይችላል። ይህ ምስክርነት የሃኪሞችን፣ የፖሊስ አባላትን እና ድርጊቱ ሲፈጸም የተመለከቱ በአከባቢው የነበሩ ሰዎችን ይጨምራል።
የቀድሞ የፖሊስ አባል ጆርጅ ፍሎይድን ለመግደል ሳያሴር ሕይወቱን አጥፍቷ በሚል ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የሚገኝ ከሆነ እስከ 40 ዓመት እስር ሊፈረድበት ይችላል።