ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ሕንድ ዕድሜያቸው ከ18 በላይ ለሆኑ ዜጎቿ የኮቪድ ክትባት ልትሰጥ ነው
ሕንድ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የክትባት መርሀ ግብሯን በስፋት ማዳረስ ጀምራለች።
ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሁሉም አዋቂዎች በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ወር የመጀመሪያ ቀን ላይ ክትባቱን መውሰድ እንደሚጀምሩ ተገልጿል።
ነገር ግን በሕንድ በበርካታ ግዛቶች የክትባት እጥረት መኖሩ ችግር ሊሆን እንደሚችል የተገመተ ሲሆን ተጨማሪ ክትባቶችን መንግሥት ከየት ሊያቀርብ እንደችሚል የተገለጸ ነገር የለም።
የሕንድ መንግሥት ባለፈው ሳምንት እንዳለው 27 ሚሊዮን የክትባት ብልቃጦች ብቻ ነበር ያሉት። ይህ ማለት ደግሞ አሁን አገሪቱ ዜጎቿን እየከተበችበት ካለው ፍጥነት አንጻር ለ9 ቀናት ብቻ የሚበቃ ነው ማለት ነው።
ሕንድ በአሁኑ ሰዓት የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ዕድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ የሆኑ ዜጎቿን በበርካታ ግዛቶች እየከተበች ሲሆን የክትባት እጥረት ግን እንዳጋጠመ ተገልጿል። ጥቂት በማይባሉ ግዛቶችም ክትባቱን ለመስወድ የመጡ ሰዎች ሰይከተቡ መመለሳቸው ተዘግቧል።
እንደ ሴረም ያሉ ትልልቅ የክትባት አቅራቢ ድርጅቶች በመላው ዓለም ያለውን የክትባት ፍላጎት ማርካት እንደከበዳቸውና ክትባቱን ለማምረት የሚውሉ ጥሬ እቃዎች እጥረት እንዳጋጠማቸውም ገልጸዋል። ይህም የሆነው አሜሪካ ክትባቱን ለማምረት የሚውሉ ጥሬ እቃዎች ወደሌላ አገራት እንዳይላኩ በማገዷ ነው።
በሕንድ ክትባቱ ሲሰጥበት የነበረው መንገድ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ነበር፤ ነገር ግን መንግሥት ሕጉን በመቀየር ላይ ነው። ይህ ለውጥም የክትባት ምርት እና አቅርቦትን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምረው ታምኖበታል።
የሕንድ የክትባት አምራቾች አገሪቱ ከሚያስፈልጋት 50 በመቶ የሚሆነውን ለማዕከላዊ መንግሥት ማቅረብ ያለባቸው ሲሆን ቀሪው 50 በመቶ ደግሞ በግዛቶችና በነጻ ገበያ ዋጋው የሚወስ ይሆናል።
መጀመሪያ ላይ በሕንድ ሶስት ክትባቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቃድ አግኝተው ነበር። ሁለቱ ክትባቶች በሕንድ ክትባት አምራች ድርጅቶች ሴረም ኢንስቲትዩትና ባራት ባዮቴክ የተዘጋጁ ሲሆን ሶስተኛ ደግሞ የሩሲያው ስፑትኒክ ቪ ነው። መንግሥት ግን በሌሎች አገራት ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ተጨማሪ ክትባቶቸ በሕንድም ይጀመራሉ ብሏል።
በተጨማሪም መንግሥት ለሁለቱ የሕንድ ክትባት አምራች ድርጅቶች 600 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጓል።
ሕንድ ከያዝነው ወር ጀምሮ እስካሁን በየቀኑ ቢያንስ 200 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙባት እንደሆነ ሪፖርት አድርጋለች። በሕንድ ከአንድ ዓመት በፊት በየቀኑ 93 ሺ ሰዎች ነበር የሚያዙት።
የሟቾችም ቁጥር ቢሆን አየጨመረ ነው። ትናንት ሰኞ ዕለት ብቻ በሕንድ 1 ሺ 619 ሰዎች በኮሮረናቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸው እንዳለፈ መንግሥት አስታውቋል።