የኬፕ ታውን ነዋሪዎች ሰደድ እሣት ሽሽት ከተማዋን ለቀው እየወጡ ነው

የደቡብ አፍሪካ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች 17 ፎቅ ያላቸው ሶስት አፓርትማዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን አስወጥተዋል።

ቴብል የተባለው ተራራ ላይ የተነሳውን ሰደድ እሣት ፍራቻ በርካቶች ከተማዋን ለቀው እየወጡ ይገኛሉ።

እሣቱ የተነሳው እሑድ ጥዋት ለፖለቲከኛዋ ሴሲል ሮዴዥ በተሠራው መታሰቢያ አቅራቢያ ነው።

ሰደድ እሣቱ አንድ ምግብ ቤትን ሙሉ በሙሉ አውድሟል። የኬፕ ታውን ዩኒቨርሲቲ ታሪካዊ ቤተ-መፃሕፍትም ክፉኛ ተጎድቷል።

250 ያክል የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በነፋስ እየተገፋ በመስፋፋት ላይ ያለውን ሰደድ ለመግታት እየተሯሯጡ ይገኛሉ።

በግዙፍ ጋሎን ውሃ የተሸከሙ ሄሊኮፕተሮች እሣቱን ለማጥፋት ጥረት ቢያደርጉም እስካሁን ብዙ አልተሳካላቸውም።

የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ፓርኮች ድርጅት እንደሚለው የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ጥቆማ የደረሳቸው እሁድ ጥዋት 1፡00 ሰዓት ነው።

የፓርኮች ድርጅት እንደሚለው እሣቱ በፍጥነት እየተስፋፋ ያለው የአየር ሁኔታው ነፋሻማ እንዲሁም ሳሮች በመድረቃቸው ነው።

ቴብል ተራራ ብዙ ጊዜ የእሣት አደጋ ያጋጥመው እንጂ በአቅራቢያው ወዳለው ዩኒቨርሲቲ ሲዛመት ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የከተማዋ ባለሥልጣናት እንደሚሉት እሣት አደጋውን ሆን ብሎ ነው ያስነሳው የተባለው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ውሏል

"እሣቱ በቁጥጥር ሥር አልዋለም። ለዚህ ደግሞ ነፋሱ አስተዋፅዖ እያደረገ ነው" ይላል የከተማዋ አስተዳዳሪዎች የለቀቁት መግለጫ።

የአደጋ ጊዜ ሰዎች በቴብል ተራራ አቅራቢያ ያሉ ነዋሪዎችን ከቤታቸው ማስወጣት ጀምረዋል።

ከመሃል ከተማው ወጣ ብሎ ያሉ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ወደ ቤታቸው እንዲልኩ ታዘዋል።

ሶስት ተመሳሳይ መኖሪያ ሕንፃዎች የተሰደሩበት ዲሳ ፓርክ የተሰኘው የመኖሪያ መንደር ሰዎችም እንዲሸሹ ተነግሯቸዋል።

የኬፕ ታውን ዪኒቨርሲቲ በመዘጋቱ 4 ሺህ ገደማ ተማሪዎች ከአካባቢው እንዲሸሹ ተደርገዋል።

ሰደድ እሣቱ 200 ዓመት ዕድሜ ያለውን የጃገር ቤተ-መፃሕፍት ማንበቢያ ክፍል እንዲሁም በርካታ የአፍሪካ ታሪካዊ መፃሕፍትን አውድሟል።

ነገር ግን አንዳንድ ታሪካዊ ቁሶች በእሣት አደጋው ከመበላት ተርፈዋል።

የዩኒቨርሲቲው እሣት ተከላካይ በሮች በመዘጋታቸው በርካታ ታሪካዊ የዩኒቨርሲተው ታሪካው ስብስቦች ከእሣት አደጋው አምልጠዋል።

ነዋሪዎች ጭስ ወደ ቤታቸው እንዳይገባ በር እና መስኮቶቻቸውን ዘግተው ተቀምጠዋል።

የእሣት አደጋ ሰዎች ሰደዱን ለማጥፋት ቢያንስ ሶስት ቀናት ያስፈልጋቸዋል እየተባለ ነው።