በግብጽ በደረሰ የባቡር አደጋ ቢያንስ የ32 ሰዎች ሕይወት አለፈ

በግብጽ ያጋጠመው ባቡር አደጋ

የፎቶው ባለመብት, EPA

በግብጽ ባጋጠመ የባቡር አደጋ ቢያንስ 32 ሰዎች ሲሞቱ ከ100 በላይ ደግሞ መጎዳታቸውን የአገሪቱ የባቡር ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ።

አደጋው ተከሰተው ሁለት የመንገደኛ ባቡሮች በተጋጩበት ጊዜ ሁለት ፉርጎዎች ከሃዲዳቸው ወጥተው በመገልበጣቸው ነው።

የትራንስፖርት ባለስልጣኑ እንዳለው ከሆነ፤ ከፊት የነበረው ባቡር የአደጋ ጊዜ ፍሬን "ማንነታቸው ባልታወቀ ግለሰቦች" በመያዙ ከኋላ የነበረው ባቡር ከፊተኛው ባቡር ጋር ሊጋጭ ችሏል።

የአገሩቱ ባለስልጣናት በአደጋው ዙሪያ ተጨማሪ ምርመራዎችን እያካሄዱ ይገኛሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለአደጋው ተጠያቂ ሆኖ በሚገኝ አካል ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድ ፕሬዝደንት አብዱልፋታህ አልሲሲ ተናግረዋል።

"በቸልተኝነት፣ በሙስናም ሆነ በማናቸውም ምክንያት ለዚህ አደጋ መንስዔ የሆነ ሰው፤ ያለ አንዳች መዘግየት ከፍተኛውን ቅጣት መቀጣት አለበት" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ፕሬዝደንት ሲሲ ጽፈዋል።

የደረሰውን አደጋ የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ሁለት ፉርጎዎች የውሃ አካል አቅራቢያ ተገልብጠው አሳይተዋል።

የአገሪቱ ጤና ሚንስቴር በአደጋው ከሞቱት ባሻገር በ108 ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ማጋጠሙን አስታውቋል።

ከባቡሩ ፉርጎ ሥራ መውጣት ያልቻሉ ሰዎችን ለማግኘት ክሬኖች እንደሚያስፈልጉ እና ሰዎችን በፍጥነት ከአደጋው ቦታ ማንሳት ባለመቻሉ የሰዎች ሕይወት ስለማለፉ ሬውተርስ በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ጠይቆ ዘግቧል።

የግብጽ መገናኛ ብዙሃን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሙስጠፋ ማድባውለይ አደጋው ወደ አጋጠመበት ስፍራ እየተጓዙ እንደሆነ ዘግበዋል።

ግብጽ ለባቡር መስመሮቿ ጥብቅ ጥገና ባለማድረጓ በባቡር መስመሮቿ ላይ ተደጋጋሚ አደጋ ያጋጥማታል።

እአአ 2002 ወደ ደቡባዊ ካይሮ እየተጓዘ በነበረ ባቡር ላይ ባጋጠመ የእሳት አደጋ 373 ሕይወታቸውን አጥተው ነበር።