ኢትዮጵያ ጫፍ በደረሰችበት የአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፉ ሰባት አገራት ትላንት ተለዩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትላንት በተካሄደ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ወደ በካሜሮን አዘጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚሳተፉ ተጨማሪ ሰባት አገራት ተለዩ።
ጋምቢያ፣ ኮሞሮስ፣ ጋቦን፣ ጋና፣ ግብጽ፣ ዚምባብዌ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ናቸው ወደ አህጉራዊው ውድድር ማለፋቸውን ያረጋገጡት አገራት ናቸው።
ጋምቢያ አንጎላን በሜዳዋ 1 ለ 0 በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድር አልፋለች።
በምድብ አራት የምትገኘው ጋምቢያ ከሁለቱ አላፊ ቡድኖች አንዷ የሚያደርጋትን ወሳኝ ጎል አሳን ሴሳይ ከዕረፍት መልስ አስገኝቷል።
በዚህ ምድብ የምትገኘው ጋቦን ዲሞክራቲክ ኮንጎን 3 ለ 0 በማሸነፍ ሌላኛዋ አላፊ አገር ሆናለች። በዚህም ጋቦን የ2019ኙ ውድድር ካመለጣት በኋላ ወደ ውድድር መድረኩ ለመመለስ በቅታለች።
ፒየር-ኤሚሪክ ኦባሜያንግ፣ ዴኒስ ቡዋንጋ እና አሮን ቡውፔንዛ ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።
ባለፉት 4 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ተሳትፋ የነበረውች ኮንጎ፤ ከምድቧ ሳታልፍ ቀርታለች።
በካሜሩን አዘጋጅነት ለመኪሄደው ውድድር ለማለፍ በምድብ 6 የምትገኘው ግብጽ የሚያስፈልጋትን አንድ ነጥብ ለማግኘት ከኬንያ ጋር ተጫውታ 1 ለ 1 አቻ ተለያይታለች።
ፈርኦኖቹ ከኮሞሮስ ጋር እኩል ዘጠኝ ነጥብ ይዘዋል። ኬንያ አራት ነጥብ ሲኖራት ቶጎ በሁለት ነጥብ በምድቡ ግርጌ ላይ ትገኛለች።
በናይሮቢ በተካሄደው ጨዋታ ማግዲ አፍሻ በሁለተኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል ግብጽ ቀዳሚ ሆናለች። ከእረፍት መልስ ኬንያ በአብደላህ ሃስ አማካኝነት አቻ ለመሆን ችላለች።
ቀድም ብላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ መሳተፏን ያረጋገጠችው ኮሞሮስ ከሜዳዋ ውጪ ከቶጎ ጋር 0 ለ 0 ተለያይታለች።
ከዚህ በፊት በውድድሩ መሳተፍ ያልቻሉት ቡድኖች ከ2019 ጀምሮ 16 የነበረው የተወዳዳሪ አገራት ቁጥር ወደ 24 በማደጉ ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል።
ከምድብ ሦስት ለማለፍ ከደቡብ አፍሪካ ጋር 1 ለ 1 በሆነ ውጤት አቻ በመውጣት ጋና ወደ ውድድሩ የሚያስገባትን ትኬት ቆርጣለች።
መሐመድ ቁዱስ ከ2010 የዓለም ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ በኡራጓይ ተሸንፈው በወጡበት ስታዲየም ቀዳሚ የሚያደርጋቸውን ጎል ቢያስቆጥርም በደቂቃዎች ልዩነት ፐርሲ ታው ደቡብ አፍሪካን አቻ አድርጓል።
ካለፉት 15 ውድድሮች በአንዱ ብቻ ያልተካፈሉት ጥቁሮቹ ከዋክብት አስር ነጥብ በመያዝ ከደቡብ አፍሪካ እኩል ሆነዋል። በስድስተኛው እና በመጨረሻው የምድቡ ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ ዘጠኝ ነጥብ ካላት ሱዳን ጋር ትጫወታለች።
ጋና ከሱዳንም ሆነ ከባፋና ባፋናዎች ጋር በነበራት ጨዋታ ያላት ውጤት የተሻለ በመሆኑ የአራት ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮኗ ከውድድሩ ውጭ የምትሆንበት ሁኔታ የለም።
ዚምባብዌ ከሜዳዋ ውጪ ቦትስዋናን 1 ለ 0 አሸንፋለች። አልጄሪያ በሌላ የምድቡ ጨዋታ ከዛምቢያ ጋር 3 ለ 3 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቃለች። በዚህም ዚምባብዌ እና አልጄሪያ ተያይዘው ሲያልፉ የ2012ቱ ውድድር አሸናፊ ዛምቢያ ከውድድሩ ውጪ ሆናለች።
ኤሚሊዮ ንሱ በመጨረሻው ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል ኢኳቶሪያል ጊኒ ታንዛኒያን 1ለ 0 በማሸነው ማለፏን አረጋግጣለች።
ሊቢያን 5 ለ 2 በሆነ ውጤት ያሸነፈችው ቱኒዚያ ከምድብ አንድ ቀድማ ነበረ ለውድድሩ ማለፏን ያረጋገጠችው። በከፍተኛ ጎል ልዩነት ቢሸነፉም ሊቢያውያን ከሰባት ዓመታት እገዳ በኋላ ብሔራዊ ቡድናቸውን በሜዳው ሲጫወቱ ለማየት በመቻላቸው ተደስተዋል።
በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው ውድድር ላይ ከሚሳተፉ ቡድኖች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተለይተዋል። ኮሞሮስ፣ ጋቦን፣ ጋምቢያ፣ ጋና፣ ግብጽ፣ ዚምባብዌ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ አልጄሪያ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒ፣ ማሊ፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዝያ እና አስተናጋጇ ካሜሩን በውድድሩ መሳተፋቸውን አረጋግጠዋል።
ኢትረዮጵያስ ምን ተስፋ አላት?
በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከኮትዲቯር፣ ማደጋስካር እና ኒጀር ጋር የተመደበችው ኢትዮጵያ፤ በመጀመሪያው ጨዋታ በማደጋስካር አንድ ለባዶ ተሸንፋ የነበረ ሲሆን፤ በቀጣይ በባሕር ዳር በተደረገ ጨዋታ ኮትዲቯርን ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችላለች።
በመቀጠል ዋልያዎቹ ወደ ኒጀር ተጉዘው፤ አንድ ለባዶ ቢሸንፉም በመልሱ ጨዋታ ሦስት ለባዶ ማሸነፍ ችለዋል።
ዋልያዎቹ ከማደጋስካር ጋር በነበራቸው የምድብ ጨዋታ ደግሞ አራት ለባዶ በማሸነፍ ነው ምድቡን በዘጠኝ ነጥብ መምራት የቻሉት።
በምድቡ ወሳኝ ጨዋታ ዛሬ ኮትዲቯር ከኒጀር የሚያደርጉት ሲሆን ጨዋታው በኮትዲቯር አሸናፊነት የሚጠናቀቅ ከሆነ ኢትዮጵያ በምድቡ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ትላለች።
ጨዋታው በኒጀር አሸናፊነት አልያም አቻ የሚጠናቀቅ ከሆነ ደግሞ ዋልያዎቹ መሪነታቸውን አስጠብቀው ወደ መጨረሻው የምድብ ጨዋታ ይጓዛሉ ማለት ነው።
ዋልያዎቹ በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታቸውን መጋቢት 21/2013 ዓ.ም በኮትዲቯር የሚያደርጉ ሲሆን ማደጋስካር ከኒጀር የሚያደርጉትም ጨዋታ በጉጉት የሚጠበቅ ነው።
ኢትዮጵያ ኮትዲቯርን የምታሸንፍ ከሆነ በካሜሩን አዘጋጅነት በሚካሄደው ጨዋታ ተሳታፊነቷን የምታረጋግጥ ሲሆን፤ ማደጋስካር ከኒጀር የሚያደርጉት ጨዋታ በኒጀር አሸናፊነት የሚጠናቀቅ ከሆነ ደግሞ ሰፊ የማለፍ ዕድል ይኖራታል።
ዋሊያዎቹ ለመጨረሻው የምድቡ ቸዋታ ዛሬ ኮትዲቯር አቅንተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም የብሔራዊ ቡድን አባላት "ከተለያዩ አካባቢዎች እና ቡድኖች የመጡ ተጨዋቾች በአንድ ዓላማ ተጫውተው ያስገኙት ድል ትልቅ አርአያነት አለው" በማለት እስካሁን ያስመዘገቡትን ውጤት አድንቀው ለቀጣዩ ጨዋታ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
33ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት መራዘሙ ይታወሳል።












