ኮሮናቫይረስ፡ ኬንያ በናይሮቢና በሌሎች ግዛቶቿ ጥብቅ የኮቪድ-19 ክልከላዎችን ጣለች

ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ

የፎቶው ባለመብት, State House Kenya

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ

ኬንያ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰውን የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመቆጣጠር መዲናዋ ናይሮቢን ጨምሮ በአምስት ግዛቶች ጥብቅ የኮቪድ-19 መቆጣተሪያ ክልከላዎችን ጣለች።

ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያት በአገሪቱ በተለይም የኮቪድ-19 ክልከላዎች በተጣለባቸው ግዛቶች የኮሮናቫይረስ ስርጭት በፍጥነት እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሬዘደንቱ እንዳሉት ባለፉት ሦስት ወራት በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2 በመቶ ወደ 22 በመቶ ከፍ ብሏል ያሉ ሲሆን፤ በየቀኑ 7 ሰዎች ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው እንደሚያልፍ አመልክተዋል።

ፕሬዝደንቱ በናይሮቢ፣ በካጂያዶ፣ በኪያምቡ፣ በማቻኮስ እና በናኩሩ ግዛቶች እና ከግዛቶቹ ውጪ የሚደረጉ ማናቸውም አይነት ጉዞዎችን አግደዋል።

ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እንዲዘጉም ወስነዋል። በምግብ ቤቶች ውስጥ ተቀምጦ መመገብ ተከልክሏል። መጠጥ ቤቶችም አልኮል መሸጥ አይችሉም ብለዋል ፕሬዝደንቱ።

ከዚህ በተጨማሪ ፕሬዝደንቱ ከዚህ ቀደም ከምሽቱ አራት ሰዓት ይጀምር የነበረው ሰዓት እላፊን በማሻሻል ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋት 10 ሰዓት የሚዘልቅ እንዲሆን አውጀዋል።

የአገሪቱን ፓርላማም ላልተወሰነ ጊዜ በእረፍት ላይ እንዲቆይ ጠይቀዋል። በሐይማኖት ተቋማትም ሰዎች በጋራ ተሰብሰበው መጸለይ ወይም ማምለክ አይችሉም ሲሉ አውጀዋል።

የግል እና የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞችም ከቤት ሆነው እንዲሰሩ ፕሬዝደንቱ የጠየቁ ሲሆን፤ በቀብር ሥነ-ሥርዓት ላይም ከ50 ያልበለጡ፤ በሠርግ እና መሰል ሥነ-ሥርዓቶች ላይ ደግሞ ከ30 ያልበለጡ ሰዎች ብቻ እንዲገኙ አዘዋል።

ኬንያ አስትራዜኔካ ሰራሹን የኮቪድ-19 ክትባት ለዜጎቿ መስጠት የጀመረች ሲሆን፤ ክትባቱ እድሜያቸው ከ58 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ፕሬዝዳንቱም በዛሬው ዕለት የወረርሽኙን መከላከያ ክትባት በቀጥታ በቴሌቪዥን እየታዩ ወስደዋል።