ባይደን ከአፍሪካ ህብረት ጋር ያለውን ግንኙነት እንደገና ለማጠናከር ቃል ገቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አገራቸው ከአፍሪካ ህብረት ጋር ያላትን አጋርነትና ግንኙነት ለማጠናከር ቃል ገቡ።
ስልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ የመጀመሪያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን በተመለከተ ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግር ነው ይህንን ያሳወቁት።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2018 የአፍሪካ አገራትን አፀያፊ በሆነ መልኩ በመስደባቸው ከፍተኛ ውርጅብኝን ማስተናገዳቸው የሚታወስ ነው።
ከአፍሪካ አህጉር የሚመጡ ስደተኞች ቆሻሾች ናቸው ማለታቸውን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል ብሎ ነበር።
ሆኖም ትራምፕ ዘረኛ አይደለሁም በማለት ይከራከራሉ።
በዛሬው ዕለት ዋይት ሃውስ የፕሬዚዳንቱን መልዕክት ባወጣው ቪዲዮ
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
"የኔ አስተዳደር አሜሪካ በአለም ላይ ያለንን አጋርነት ለማጠናከር እንዲሁም እንደ የአፍሪካ ህብረት ካሉ ተቋማት ጋር ያለንን ግንኙነት እንደገና ለማጠናከር እንሰራለን" በማለት በ34ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ዋዜማ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም "በአለም ላይ ያሉ ችግሮቻችንን አንድ ላይ መጋፈጥ አለብን። ለአለም አቀፉ የጤና ስርዓት የበለጠ መዋዕለ ንዋይ ልናፈስ ይገባናል፣ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መግታት፣ እንዲሁም ለወደፊቱም ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ቀውሶችን መከላከል እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ ከአፍሪካ በሽታ ቁጥጥርና ክትትል ሌሎች ተቋማት ጋር የጤና ደህንነት ጋር በተያያዘ አጋርነት መፍጠር እንፈልጋለን" ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በተጨማሪ በአህጉሪቷ የሚከሰቱ ግጭቶች ጋር በተያያዘ አገራቸው ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባባበር በበለጠ ተሳትፎ ማድረግ እንፈልጋለን ብለዋል።












