ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፖፕ ፍራንሲስ ኢንስታግራም ገጽ ሞዴሏን 'ላይክ' ካደረገ በኋላ ምርመራ ተከፈተ
የሮማ ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ ይፋዊ የኢኒስታግራም ገጽ አንድ ያልተጠበቀ ምሥልን "ላይክ" አድርጓል በሚል አዲስ ምርመራ እየተደረገበት ነው።
የሳቸው ገጽ "ላይክ" ያደረገው ምሥል ገላጣ ልብስ የለበሰች የብራዚል ሞዴል ፎቶ መሆኑ ነው ነገሩን አነጋጋሪ ያደረገው።
በፎቶው ላይ ብራዚላዊቷ ናታሊያ ጋሪቦቶ በትምህርት ቤት የደንብ ልብስ ትታያለች።
የዜና አገልግሎቶች በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ዘገባ ማቅረብ የጀመሩት ከባለፈው አርብ ጀምሮ ነው።
የሊቀ ጳጳሱ የኢኒስታግራም ገጽ ከዚህ ዘገባ መውጣት በኋላ የሞዴሏን ፎቶ "አንላይክ" አድርጎታል።
ሆኖም ይህ ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር ቻለ በሚለው ላይ ምርመራ ተጀምሯል።
የቫቲካን ቃል አቀባይ ለጋርዲያን ጋዜጣ በሰጡት ቃል "ያው ላይክ መደረጉ ከሊቀ ጳጳሳችን ባለመሆኑ ኢኒስታግራም ነገሩን እንዲመረምር ጥያቄ አቅርበናል" ብለዋል።
የሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ኢኒስታግራም ገጽ "ፍራንሲስከስ" የሚል ስም ያለው ሲሆን ከ7 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች አሉት።
የቫቲካን ከፍተኛ ኃላፊዎች ለካቶሊክ ዜና አገልግሎት ማክሰኞ ዕለት እንደተናገሩት የሊቀጳጳሱ ኢኒስታግራም አካውንት የሚንቀሳቀሰው ይህንኑ እንዲያደርጉ በተቀጠሩ ሰራተኞች ነው።
ስለዚህም ነው የውስጥ ምርመራ በመደረግ ላይ ያለው።
ብራዚላዊቷ ሞዴል በሊቀ ጳጳሱ ስም በተከፈተው ገጽ መወደዷን ተከትሎ ዝናዋ የጨመረ ሲሆን እሷም ክስተቱን ተንተርሳ ሳቅ ለመፍጠር ሞክራለች።
"በሳቸው መወደዴ ቢያንስ መንግሥተ ሰማያትን እንደምወርስ ጠቋሚ ነው" ስትልም በትዊተር ሰሌዳዋ ጽፋለች።