በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ የሆነው ምን ነበር?

ካርታ

በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ፣ ጋዋ ቃንቃ ቀበሌ በደረሰ ጥቃት ቢያንስ 32 ሰዎች በታጣቂዎች ተገድለዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ከትናንት በስቲያ፣ ጥቅምት 22/ 2013 ዓ.ም የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 32 ነው ሲል የዓይን እማኞች እና አምነስቲ በበኩላቸው የሟቾች ቁጥር ቢያንስ 54 ነው ይላሉ።

የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 32 እንደሆነ ቢጠቀስም ኮሚሽኑ ያገኛቸው መረጃዎች አሃዙ ከዛ በላይ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ ብሏል።

ይህ ግድያ የተፈጸመው ንጹሃን ዜጎች ለስብሰባ በሚል ምክንያት ተጠርተው በአንድ ስፍራ በኃይል እንዲሰበሰቡ ከተረጉ በኋላ መሆኑን የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ግድያው ማንነትን መሰረት ያደረገ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዲሁም አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ የገለፀ ሲሆን፤

ኮሚሽኑ ሶስቱ ቀበሌዎች ላይ የሚኖሩ የአማራ ነዋሪዎች ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ አስታውቋል።

አምነስቲም በመግለጫው ከ54 የማያንሱ ብሄራቸው አማራ የሆኑ ሰዎች ተገድለዋል ብሏል ትናንት ባወጣው መግለጫ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድም በበኩላቸው ግድያው ማንነትን መሰረት ያደረገ መሆኑንም የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።

የክልሉ መንግሥት ጥቃቱን ያደረሰው ራሱን ኦነግ ሸኔ በማለት የሚጠራው ቡድን ነው ብሏል።

ለመሆኑ ግድያው እንዴት ተፈጸመ?

ጥቃቱ ሲፈጸም በስፍራው የነበሩ እና ከጥቃቱ በሕይወት ያመለጡ ሁለት ነዋሪዎችን ቢቢሲ አነጋግሯል።

ያነጋገርናቸው አንድ የዓይን እማኝ የተጠራው ስብሰባ ላይ እንደነበሩና ከጥቃቱ አምልጠው አሁን ዲላ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ እንደሚገኙ ይናገራሉ።

እኚህ አርሶ አደር እንደሚሉት ታጣቂዎቹ በኃይል ሰዎችን ወደ ስበሰባው እንዲመጡ ማድረጋቸውን እና በስብሰባው ላይ "አርሶ አደር ነን የምናውቀው ነገር የለም ስንላቸው ዛሬ ጭጭ ነው የምናደርጋችሁ መውጫ የላችሁም አሉን" በማለት የተፈጠረውን ይገልጻሉ።

የዓይን እማኙ እንደሚሉት ነዋሪዎቹ በቅድሚያ በትምህርት ቤት አዳራሽ ውስጥ እንዲገቡ መደረጋቸውን ነው።

አዳራሽ ውስጥ ታጣቂዎቹ 'የጦር መሳሪያ አምጡ' እንዳሏቸው ያስረዳሉ።

"መሳሪያ የለንም ሌላ ነገር ከፈለጋችሁ እንስጣችሁ" እንዳሏቸውም እኚህ የዓይን እማኝ ይናገራሉ። ከዚያም ከአዳራሹ እንዳስወጧቸው ይናገራሉ።

የዓይን እማኙ አክለውም ከአዳራሹ ካስወጧቸው በኋላ፤ "መትረየስ አጠመዱ፣ ክላሽም አጠመዱ። ሽማግሌዎች ኧረ የነፍስ ያለህ ቢሉ አናውቅም አሉ። ጥይት አርከፈከፉብን። ሰው እንዳለ ወደቀ። የሞተው ሞተ። እንዳው ዝም ብለን ደመ ነፍሳችንን ብትንትን አልን" ብለዋል።

አክለውም "መጀመሪያ ኮማንድ ፖስት ሲጠብቀን ስለነበረ ነው እንጂ እኛም አንቀመጥም ነበር። እነሱ ልንሄድ ነው ተዘጋጁ ሳይሉን ቅዳሜ ድንገት ወጡ። ባዶ መሆናችንን ሲያውቁ ማታ ገቡ፤ የቤት እቃ፣ ስልክ ወሰዱ። እሁድ ሸኔዎቹ መጥተው አደጋ አደረሱብን" ሲሉም ተናግረዋል።

እሳቸው ከ50 በላይ አስክሬን እንዳዩ እንዲሁም ቤት መቃጠሉንም ይናገራሉ።

በአሁኑ ሰዓት ዲላ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ እንደሚገኙ እና ካምፕ ውስጥ የወረዳው አስተዳደደር ሰብስቦ ቢያስቀምጣቸውም በምግብ ተቸግረናልም ብለዋል።

ለስብሰባ በተጠራው ቦታ ነበርኩ ያለች ሌላኛዋ የዓይን እማኝ በበኩላቸው አምና የዳሯት ልጃቸውን፣ አባታቸውን እና የልጃቸው ባል አባት እንደተገደሉባቸው ይናገራሉ።

"ስብሰባ ብለው ትልቁንም ትንሹንም ጠሩ። መሣሪያ አስረክቡ አሉን። ገንዘብ፣ በሬ ወይም የፈለጋችሁትን እንስጣችሁ መሣሪያው ተለቅሞ ሄዷል አልን። በመጨረሻ እጃችንን እያርገበገብን እየለመናቸው ስብሰባ ላይ ያለነውን ፈጁ። ልጄን ከኔ ላይ ደፋት። የሷ ደም እኔ ላይ እየፈሰሰ እንደ አጋጣሚ ወጣሁ" ሲሉ ለቢቢሲ የተከሰተውን ገልጸዋል።

አሁን ከአራት ልጆቻቸው ጋር ዲላ እንዳሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል። "እህል ውሃ የለም። ሕጻናት እህል ውሃ ከቀመሱ ሦስት ቀናችን ነው" ሲሉም ያሉበትን ፈታኝ ሁኔታ ገልጸዋል።

ሁለቱም የዓይን እማኞች ጥቃቱ የተፈጸመው በቦምብ ሳይሆን "በክላሽ እና መትረየስ ነው" ይላሉ።

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ ሰኞ ረፋድ ላይ አሁን ባለን መረጃ ነዋሪዎቹ የተገደሉት በተወረወረባቸው ቦምብ ነው በማለት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

የጉሊሶ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዳግም መልካሙ በበኩላቸው ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የአማራና የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች መገደላቸውን ይናገራሉ።

"ሰዎች በአንድ ቦታ ሲገደሉ አማራዎች ብቻ አይደሉም የተገደሉት። ኦሮሞ የሆኑም ተገድለዋል። በአካባቢው ሁሉም በአንድ ላይ ተሰባጥረው ነው የሚኖሩት። በጥቃቱ የሁለቱም ብሔር ተወላጆች ተገድለዋል።" ይላሉ

ከዚህም በተጨማሪ የቀበሌ አመራሮችም ሊገደሉ ኢላማ ተደርገው ስለነበር አካባቢውን ጥለው ሸሽተው እንደነበርም ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት የተፈናቀለውን ሕዝብ ወደ ቀዬው እንዲመለስ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ዲላ ተብላ በምትጠራ ከተማ ሰፍረው እንደሚገኙም በተጨማሪ ገልፀዋል።

"የተገደሉትን መቅበር የተጎዱትን ማሳከም ላይ እንገኛለን። የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎችም ጥቃቱን ያደረሱት ላይ እርምጃ እየወሰዱ ነው" ብለዋል