አእምሮ ጤና፡ ለዓመታት ወላጆቻቸው በሰንሰለት ያሰሯቸው ናይጄሪያውያን

ለዓመታት በወላጆቻቸው ታስረው የነበሩ ሰዎች ነጻ የመውጣታቸው ዜና መላው ናይጄሪያን አስደንግጧል።
አንዳንዶቹ የአዕምሮ ህሙማን ሲሆኑ፤ በብረት ካቴና ቁርጭምጭሚታቸውን ለዓመታት ታስረዋል። በጠባብ ቦታ እንዲበሉ፣ እንዲተኙና እንዲጸዳዱም ተገድደዋል።
ከእነዚህ አንዱ የ32 ዓመት ጎልማሳ ነው። በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያዋ ካኖ ግዛት ቤተሰቦቹ ቤት ለሰባት ዓመታት ታስሮ ነበር።
የእንጀራ እናቶቻቸው ወይም ዘመዶቻቸው ያሰቃዩዋቸው ልጆችም ተገኝተዋል።
መስከረም ላይ አንድ የሰባት ዓመት ታዳጊን በመግደል እንጀራ እናቱ በቁጥጥር ስር ውላለች። እስካሁን ክስ አልተመሰረተባትም።
በዶሮ ጎጆ የታሰረው ታዳጊ
በመላው ናይጄሪያ ታዳጊዎች ጉልበታቸው እንደሚበዘበዝ ሪፖርት ይደረጋል። አሁን ግን ዋነኛው ትኩረት ያለው በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ላይ ነው።
ነሐሴ አጋማሽ ላይ በኬቢ ግዛት የ11 ዓመት ታዳጊ በዶሮ ጎጆ መታሰሩ ተሰምቷል። በቅንጡ ቤት እየኖሩ የነበሩት አባቱና እንጀራ እናቱ ለፍርድ ቀርበዋል።
ከዶሮዎች አጠገብ ተኮማትሮ የተቀመጠው ታዳጊ ምስል በርካቶችን አስቆጥቷል።

የሰብዓዊ መብት ተቋም ኃላፊው ሀሩና አያጊ፤ የታዳጊው ሁኔታ ይፋ ከተደረገ በኋላ ሌሎችም ጥቆማዎች እንደደረሷቸው ይናገራሉ።
ተቋም 12 ሰዎችን ነጻ አውጥቷል። ከነዚህ ሰባቱ ልጆች ናቸው።
"ብዝበዛ የደረሰባቸው ልጆች ከእናታቸው ጋር አይኖሩም ነበር" ይላሉ ሀሩና።
በናይጄሪያ መዲና አቡጃ ሁለት ልጆች በእንጀራ እናቶቻቸው መጸዳጃ ቤት ታስረው ተገኝተዋል።
መደብደብ፣ መቃጠል፣ መራብ
በካኖ ግዛት አንድ የሰባት ዓመት ልጅ በእንጀራ እናቷ መደብደቧ፣ መቃጠሏና ምግብም መከልከሏ ተዘግቧል።
አሁን ታዳጊዋና ሌሎችም ልጆች በመንግሥት ማቆያ ይገኛሉ። ህክምና እና የሥነ ልቦና ምክርም እየተሰጣቸው ነው።
ከልጆቹ ወላጆች መካል የታሰሩ፣ ገና ፍርድ ያልተላለፈባቸውም አሉ።
እአአ 2003 ላይ የወጣ ሕግ፤ በአግባቡ ያልተያዙ ልጆችን መንግሥት እንዲወስድ ይፈቅዳል። ሆኖም ካኖን ጨምሮ 11 የናይጄሪያ ደቡባዊ ግዛቶች ሕጉን አላጸደቁም።

ሕጉ ከ18 ዓመት በታች ያሉ ልጆች ማግባት አይችሉም ስለሚል ተቃውሞ ገጥሞታል። አንዳንድ የሙስሊም ማኅበረሰብ ለአቅመ አዳምና ሔዋን የደረሱ ልጆች መዳር አለባቸው ይላል።
ሕጉ አለመጽደቁ ብዝበዛ የሚደርስባቸውን ልጆች መንግሥት እንዳይታደግ እንቅፋት ሆኗል።
በአካባቢው ከአንድ ሚስት በላይ ማግባት የተለመደ ነው። ይህ ማለት በርካታ ልጆች ከእናቶቻቸው ጋር አይኖሩም ማለት ነው። ከወላጅ እናታቸው ተነጥነው ለእንግልት ይዳረጋሉ።
የሴቶችና ሕፃናት መብት ታጋይ ተቋም መሪዋ ላማቦግ ላዲፖ "ልጆችን ማሰቃየት እየተለመደ ነው። ሰብዓዊ መብትን ይጋፋል። ጭካኔም ነው" ይላሉ።
የታሰሩት የአዕምሮ ህሙማን
በካኖ ግዛት ቤተሰቦቹ ቤት ታስሮ የተገኘው የ30 ዓመት ግለሰብ ጎረቤቶች እንደሚሉት፤ የአዕምሮ ህመምተኛ በመሆኑ ሰባት ዓመት ታስሯል።
ግለሰቡ ሲገኝ መራመድ አይችልም ነበር።
ሌላ የ55 ዓመት የአዕምሮ ህመምተኛም በርና መስኮት በሌለው ክፍል ታስረው ተገኝተዋል። አንደኛው እግራቸው ከብረት ዘንግ ጋር ታስሮ ለ30 ዓመታት ኖረዋል።
የአዕምሮ ህሙማን ስለሚገለሉ ተገቢው እንክብካቤ አይደረግላቸውም። ቤተሰቦቻቸውም ስለማይቀበሏቸው ያረጀ ልብስ ለብሰው ከቆሻሻ መጣያ ሲመገቡ ይስተዋላል።
ዶ/ር ታይዎ ላቲፍ እንደሚሉት፤ የአዕምሮ ህሙማን ይታሰራሉ፣ እንግልትም ይደርስባቸዋል።
ምን ያህል ሰዎች የአዕምሮ ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው መረጃው የለም። ነገር ግን ከ200 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ያላቸው ከ300 ያነሰ የሥነ ልቦና ሀኪም ነው።

የፎቶው ባለመብት, HRN
የክርስትና እና እስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ባህላዊ ህክምናን ይመርጣሉ።
የአዕምሮ ህመምን ከክፉ መንፈስ ጋር የሚያስተሳስሩትም በርካታ ናቸው።
የናይጄሪያ ጤና ሚንስትር 2013 ላይ ያወጣው አሐዝ፤ ቢያንስ ዓሥር በመቶ የሚሆነው ዜጋ የአዕምሮ ህመም እንደሚገጥመው ይጠቁማል።
የዓለም ጤና ድርጅት ከነዚህ ህክምና የሚያገኙት ከ10% በታች ናቸው ይላል።
በተለይ በገጠር የሚኖሩ ሰዎች ህክምና ለማግኘት ይቸገራሉ።
ሆኖም የአዕምሮ ህክምና መስጫ ባለባቸው ቦታዎችም ሳይቀር ህሙማን ይገለላሉ።
"ብዙ ሰዎች የአዕምሮ ህክምና መስጫ ሲገቡ መታየት አይሹም። ብዙ የተዛቡ አመለካከቶች ከአዕምሮ ህመም ጋር ተያይዘዋል። ሰዎች የአዕምሮ ህመም እንዳለባቸው መካድን ይመርጣሉ" ይላሉ ዶ/ር ታይዎ።


















