ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስዊዘርላንድ ድንበሯን ከአውሮጳ ኅብረት በመዝጋት ጉዳይ ላይ ሕዝበ ውሳኔ አካሄደች
ስዊዝ ድምጽ ሰጪዎች በከፍተኛ ድምጽ ሐሳቡን ውድቅ አድርገውታል።
የአውሮጳ ኅብረት አገራት ሰዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቅደውን ሕግ ለመቀልበስ ነበር ሕዝበ ውሳኔው የተካሄደው።
ድምጽ ከሰጡት ውስጥ 62% የሚሆኑት ከአውሮጳ አባል አገራት ጋር ነጻ እንቅስቃሴ ይቀጥል ያሉ ሲሆን 38% የሚሆኑት ብቻ ድንበራችንን እንዝጋ ብለዋል።
ስዊዘርላንድ የአውሮጳ ኅብረት አባል አገር አይደለችም። ነገር ግን ከኅብረቱ ጋር በርካታ የትብብር ስምምነቶችን ታደርጋለች። ከብራስልስ ጋር በቅርብ ትሰራለች። ይህም የአውሮጳ ነጻ የንግድ ቀጠና ተሳታፊ እንድትሆነ አስችሏታል።
ድንበራችንን ጠርቅመን እንዝጋ የሚለው ሐሳብ ለሕዝብ ውሳኔ የቀረበው የስዊዝ ፒፕልስ ፓርቲ ወይም በምኅጻረ ቃሉ ኤስቪፒ ተብሎ የሚጠራው የፖለቲካ ድርጅት ባቀረበው ሐሳብ መሠረት ነው።
በተመሳሳይ ሁኔታ ከ6 ዓመት በፊት ስደተኞችን ከአውሮጳ ኅብረት በኮታ በመቀበል ጉዳይ ላይ ሕዝበ ውሳኔ ተደርጎ ነበር።
በስዊዘርላንድ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙርያ ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ የተለመደ ተግባር ነው። ቀጥተኛ ዲሞክራሲን በማራመድ የምትታወቀዋ ስዊዘርላንድ በአካባቢያዊና በአገራዊ ጉዳዮች ሕዝቡ ምን እንደሚፈልግ የሚጠየቀው በተወካዮቹ ሳይሆኑ በቀጥታ ድምጽ በመስጠት ነው።
ነጻ እንቅስቃሴ መኖር የለበትም የሚሉ ወገኖች ስዊዘርላንድ ድንበሮቿን ሙሉ በሙሉ እንድትቆጣጠርና የምትፈልጋቸው ስደተኞች ብቻ አገራችን እንዲገቡ ማድረግ እንችላለን ብለው ያምናሉ።
ከአውሮጳ አገራት ጋር ነጻ እንቅስቃሴ ሊቀጥል ይገባል የሚሉት ደግሞ አሁን ያለውን ጤናማ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ያውካል፣ በሺ የሚቆጠሩ የስዊዝ ዜጎች በሌሎች የአውሮጳ አገራት እንደልብ ተንቀሳቅሰው ለመስራት እንዳይችሉ ያደርጋል ሲሉ ቆይተዋል።
ስዊዘርላንድ ወደብ አልባ ሀብታም አገር ስትሆን ለብዙ ዓመታት በዓለምና አካባቢያዊ ፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ በመሆን ትታወቃለች።