ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትግራይ ምርጫ፡ "በእጩዎቻችንና በቤተሰቦቻቸው ላይ ማስፈራርያ ደርሷል" ሳልሳይ ወያነ ትግራይ
የትግራዩ ተቃዋሚ ፓርቲ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት) ዛሬ [ሰኞ ጠዋት] በሰጠው መግለጫ፣ በምርጫው ሂደት በተወዳዳሪዎቹና በታዛቢዎቹ ላይ "ማስፈራርያና ጫና" ይደርስ እንደነበረ አስታወቀ።
ፓርቲው እንዳለው ተገቢ ያልሆኑ ነገሮች ከምርጫው ቀን በፊት አንስቶ ይስተዋሉ እንደነበር ጠቅሶ፤ በዚህም የገዢው ፓርቲ አባላት ከምርጫው በፊት ቤት ለቤት እየዞሩ "ምልክት የምታደርጉት እዚህ ላይ ነው" በማለት በመራጮች ላይ ጫና ሲያሳድሩ እንደነበር ገልጿል።
በተጨማሪም ሳልሳይ ወያነ ትግራይ በመግለጫው ላይ እንዳለው በተወዳዳሪዎቹ እና ታዛቢዎቹ ላይ "ማስፈራርያና ጫና" እንደደረሰም አመልክቷል።
"የወረዳና የቀበሌ መዋቅሮችን በመጠቀም፣ በእጩ ተመራጮቻችን እና ቤተሰቦቻቸው ላይ ማስፈራርያ ይደርስ ነበር፤ በሕዝብ እንደ ጠላት እንዲታዩና እንዲሸማቀቁም ሲደረግ ነበር" ብሏል።
ከዚህ ባሻገርም፣ ገዢው ፓርቲ "በሚድያና በሰነድ የተደገፈ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ አካሂዶብናል" ሲልም ፓርቲው ከሷል።
ድምጽ በሚቆጠርበት ወቅት፣ ታዛቢዎቹን ከምርጫ ጣብያው ለማራቅ የተደረጉ ጫናዎች እንደነበሩም ነው የገለጸው።
ፓርቲው፤ ምርጫው እንዲካሄድ ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱን እና ምርጫውም "ታሪካዊ" እንደነበር በመግለጫው አትቷል።
ምርጫው በመካሄዱም ደስተኛ መሆኑን ገልጾ "[የትግራይ ሕዝብ] በመስዋዕትነቱና በድሉ ያረጋገጠውን የራስን ዕድል በራስ የመወሰንን መብት ለድርድር እንደማያቀርብ ለዓለም ያስመሰከረበት በመሆኑ ኩራት ይሰማዋል" ብሏል በመግለጫው።
ነገር ግን፣ ከምርጫው በፊትና በምርጫው ወቅት ነበሩ ያላቸውን "እጥረቶችና እንቅፋቶችን" ዘርዝሯል።
በትግራይ ክልላዊ ምርጫ ህወሓትን ጨምሮ አምስት ፓርቲዎች በምርጫው ላይ መሳተፋቸው ይታወሳል።
የፌደራሉ መንግሥት ሕገወጥና ተቀባይነት የለውም ባለው፤ በትግራይ ክልል ጳጉሜ አራት በተካሄደው በዚህ ክልላዊ ምርጫ ህወሓት በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፉ ይታወቃል።