የኮሮናቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ

ኮሮናቫይረስ በዓለምአቀፍ ደረጃ ሊሰራጭ የሚችልበት እድል በጣም ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን ባደረገው የአደጋ ምዝና ማረጋገጡን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

ቢሆንም ግን አሁንም የቫይረሱን የስርጭት ገመድ የመበጠስ እድል እንዳለ መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በዚህ ጊዜ ፍርሃትና የተሳሳቱ መረጃዎች ትልቅ ተግዳሮት እንደሚሆኑ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት 50 የሚሆኑ አገራት ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች እንዳገኙ ሪፖርት አድርገዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ ጤና አደጋዎች መርሃግብር ሃላፊ ማይክ ራያን እንደሚሉት የቫይረሱ ስርጭት ደረጃው መንግሥታት በተግባር ቫይረሱን ለመቆጣጠር እያደረጉ ያለውን ነገር ለመገምገም ይረዳቸዋል።

የአገራት የጤና ተቋማት ዝግጅት እስካሁንም እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነም ጠቅሰዋል።

ከዚህም ባለፈ "ለአገራችሁ ዜጎች ስትሉ የመዘጋጀት ግዴታ አለባችሁ፤ ለቀሪው ዓለም ስትሉም የመዘጋጀት ግዴታ አለባችሁ" በማለት ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያቸውን ለመንግሥታት አስተላልፈዋል።

በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት ያለው መረጃ ቫይረሱ ዓለምአቀፍ ወረርሽኝ አለመሆኑን እንደሚያሳይ ገልፀዋል።

"ወረርሽኝ ሆኗል ካልን እዚህ ፕላኔት ላይ ያለ ማንኛውም ሰው ተጋላጭ እንደሆነ መቀበላችን ነው። ያለን መረጃ ግን ይህን አያረጋግጥም" በማለት አብራርተዋል።

ዶ/ር ቴዎድሮስ በበኩላቸው "በአሁኑ ወቅት ትልቁ ጠላታችን ቫይረሱ ሳይሆን ፍርሃት፣ ሃሰተኛ መረጃዎችና ማግለል ናቸው" ብለዋል።

ተቋማቸው የዓለም ጤና ድርጅት ሁሉም መንግሥታት፤ ሁሉም ማህበረሰብ በተገቢ መንገድ ቫይረሱን ለመቆጣጠር ቢሞክር ስርጭቱን ለመግታት ብሎም የስርጭት መስመሩን ለመስበር እንደሚያስችል አስታውቋል።